አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዛሬም ወደፊትም ኢትዮጵያ በመሥዋዕትነት ፀንታ ትኖራለች ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡
አገልግሎቱ 87ኛውን የየካቲት 12 ሰማዕታት መታሰቢያ ቀን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው÷ ኢትዮጵያ በጋራ ተጋድሎ ዳር ድንበሯንና ሰንደቋን የማስከበርና የነፃነት ታሪክ እሴት ያላቸው ሕዝቦች ሀገር ናት፡፡
በየዘመኑ የሚከፈለውን መሥዋዕትነት ሁሉ ከፍለው ክብሯንና ሰንደቋን ከፍ የሚያደርጉ ጀግኖች ልጆች ነበሯት፤ ዛሬም አሏት፤ ወደፊትም ይኖሯታልም ነው ያለው፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ዛሬም ወደፊትም ኢትዮጵያ በመሥዋዕትነት ፀንታ ትኖራለች
ኢትዮጵያ በጋራ ተጋድሎ ዳር ድንበሯንና ሰንደቋን የማስከበርና የነፃነት ታሪክ እሴት ያላቸው ሕዝቦች ሀገር ናት፡፡ በየዘመኑ የሚከፈለዉን መሥዋዕትነት ሁሉ ከፍለዉ ክብሯንና ሰንደቋን ከፍ የሚያደርጉ ጀግኖች ልጆች ነበሯት፤ ዛሬም አሏት፤ ወደፊትም ይኖሯታል፡፡
ሀገራቸው ስትነካ ከየአቅጣጫዉ ተሰባስቦ በኅብር የሀገራቸውን ሉዓላዊነትና ክብር ማስጠበቅ በየትውልዱ የቀጠለ የኢትዮጵያዊያን አኩሪ ታሪክ ነው፡፡
ፋሽስት ጣሊያን በቅኝ ግዛት ዘመን የደረሰበትን የዓድዋ ሽንፈት ለመበቀል በ1928 ዓ.ም ድጋሚ የወረራ ሙከራ አድርጎ ነበር፡፡ ለአምስት ዓመታት በቆየዉ ወረራ በመላዉ ኢትዮጵያ ወራሪዉ ፋሽስት የቆየው የእሳት ፍም ላይ እንደቆመ ሆነው በየቦታዉ በጀግኖች አርበኞች ሲቆላ ነበር፡፡ በአንጻሩ የፋሽስቱ መሪ ግራዚያኒ ተደላድሎ የተቀመጠ ለማስመሰል ያልተቋረጠ ሙከራ ያደርግ ነበር፡፡ የዚህ የሙከራ ተግባሩ አካል አድርጎ በአዲስ አበባ አንድ መርሃ ግብር አዘጋጅቶም ነበር፡፡ በዚህ መርሐ ግብር ላይ ኢትዮጵያዊያን አርበኞች በግራዚያኒ ላይ የተቃጣ የቦንብ ጥቃት ፈጸሙ፡፡
የዓድዋ ሽንፈቱን ለመበቀል ተጨማሪ ሰበብ ያገኘዉ ፋሽስቱ ታዲያ የበቀል ጭፍጨፋ አወጀ፡፡ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በአዲስ አበባ ብቻ ከ30 ሺህ በላይ ንጹኃን ተጨፈጨፉ፡፡ ይህ ግፍ ዘንድሮ 87ኛ ዓመቱ ነው፤ በየዓመቱም ኢትዮጵያን በደምና አጥንታቸዉ ያፀኑ ጀግኖችን ለማሰብ እንዘክረዋለን፡፡ ኢትዮጵያውያን ዕድሜ፣ ፆታ፣ ሃይማኖት፣ ብሔር ሳይለይ በግፍ ስለኢትዮጵያ ተሰውተዋልና እንዘክረዋለን፡፡
ሀገራችን በጋራ መሥዋዕትነት የተከፈለበትና የዓድዋ ጀግኖች መሥዋዕትነት በቀጣዩም ትውልድ የተደገመበት የታሪካችን አካል ሆኖ እስከ ዛሬም ይዘከራል፡፡ ኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን ደምና አጥንት የዳበረች የመሥዋዕትነታችን ውጤት ናትና የኢትዮያዊያኑ በግፍ መጨፍጨፍ አርበኝቱን አቀጣጥሎት ፋሽስትን በ1933 ዓ.ም በተባበረ ክንድ ጠራርጎ ማስወጣት ተችሏል፡፡
ኢትዮጵያ አሁንም ነፃነቷንና የግዛት አንድነቷን የሚያስከብሩ፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷን የሚያጸኑ፣ በምግብ ራስን በመቻል ሉዓላዊነቷን የሚያረጋግጡ በወል የጋራ ታሪኮቻቸዉ ላይ የፀኑ አርበኞችን በየዘርፉ እያወጣች ትገኛለች፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የዚህ ብሔራዊ አርበኝነት አካል እንዲሆንም ጥሪ ታቀርባለች፡፡
በድላችንና ነፃነታችን እየኮራን የተከፈለውን መሥዋዕተነት እየዘከርን የታፈረችና የተከበረች ኢትዮጵያን ለትውልድ እናሻግራለን፡፡
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የካቲት 12 ቀን 2016 ዓ.ም