የሀገር ውስጥ ዜና

የተጠናከረ የንቃተ ሕግ ሥራ ማከናወን በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተካሄደ

By ዮሐንስ ደርበው

February 21, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፍትሕ ሚኒስትር ዴዔታ ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) ከተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የኢትዮጵያ ተወካይ ሪታ ቢሱናውዝ (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል፡፡

ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር)÷ የሀገር አቀፍ የፍትሕ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል፡፡

በገለጻቸውም÷ የፍትሕ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግና የተገልጋዮችን እርካታ እና የሕዝቡን አመኔታ ለማሳደግ በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በዕቅዱ ከተካተቱ አምዶች ውስጥ ከድርጅቱ ጋር ተዛማጅ የሆኑና በትብብር ሊከናወኑ የሚችሉ ጉዳዮችን ለይተው በጋራ ለመስራት ከመግባባት ላይ መደረሱንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

በተለይም የተጠናከረና ሰፊ የንቃተ ሕግ ስራ ለማከናወን፣ ሃሳብን በነፃ የመግለፅ መብትን ለማስከበር እና ሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግርን ለመከላከል የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ መስጠት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

በተጨማሪም በሴቶችና ህፃነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን እንዲሁም በድረገፅ በህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለመከላከልና ግንዛቤ ለመፍጠር የሚያስችሉ ስራዎችን በሀገር አቀፍ ደረጃ በትብብር መስራት ስለሚቻልባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ ሰፊ ውይይት አድርገው ከመግባት ላይ መድረሳቸው ተጠቁሟል፡፡