የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል በተደረገው የሕግ ማስከበር ሥራ የተደቀነውን አደጋ መከላከል ተችሏል – አቶ አረጋ ከበደ

By Tamrat Bishaw

February 21, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልልን የፀጥታ ችግር ከመሰረቱ ለመፍታት የሀገር መከላከያ ሰራዊት በወሰደውና እየወሰደ በሚገኘው የሕግ ማስከበር ሥራ የተደቀነውን አደጋ መከላከል ተችሏል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ፡፡

የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የአስፈጻሚ አካላት የ6 ወራት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የክልሉን የፀጥታ ችግር ከመሰረቱ ለመፍታት በክልሉ መንግሥት ጥያቄ መሰረት የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሕግ ማስከበር ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውሰዋል።

በዚህም የተደቀነውን አደጋ መከላከል መቻሉን ገልጸዋል።

የክልሉን የፀጥታ ሁኔታ በዘላቂነት ለማጠናከርም የክልሉን የጸጥታ መዋቅር አቅም የመገንባት፣ የታጠቁ ሃይሎች በምህረት አዋጁ መሰረት በሰላም ጥሪ እንዲቀበሉ ማድረግ እንዲሁም ውጤታማ የህዝብ ውይይት መካሄዱን አንስተዋል።

በ2015/16 የምርት ዘመን በተፈጠረ የዝናብ እጥረት ምክንያት በዘጠኝ ዞኖች የተፈጠረውን ድርቅ ለመቋቋም ከክልሉ የመጠባበቂ የእህል ክምችትና ግምጃ ቤት 430 ሚሊየን ብር በመመደብ፣ ከፌዴራል መንግሥት እና ከእርዳታ ድርጅቶች የተገኘ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በግብርና ልማት፣ በኢንዱስትሪ ዘርፍ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝምና ሌሎች ዘርፎች ባለፋት ስድስት ወራት የተከናወኑ ተግባራትን ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

የክልሉ ምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ባስተላለፉት መልዕክት የክልሉ አመራር የአስተሳሰብና የጋራ አንድነት ፈጥሮ ለሰላምና ለልማት ቅድሚያ በመስጠት የክልሉን ሕዝብ ኢኮኖሚ ለማሳደግ እንዲረባረብም ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉ መንግሥት ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ቅድሚያ በመስጠት የሃሳብ ልዩነት ያላቸው ሰዎች በውይይትና ድርድር ሃሳባቸውን እንዲያቀርቡ ቅድሚያ ሰጥቶ የሚሠራ መሆኑንም አፈ ጉባኤዋ ተናግረዋል።

በደሳለኝ ቢራራ