የሀገር ውስጥ ዜና

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በሁለንተናዊ እድገት ዙሪያ ተወያየ

By Mikias Ayele

February 23, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ዛሬ ባካሄደው 3ኛ ዓመት 8ኛ መደበኛ ስብሰባው በከተማዋ ሁለንተናዊ እድገት እና የነዋሪዎች ፍላጎት ዙሪያ ተወያይቷል፡፡

ካቢኔው የከተማዋን አጠቃላይ የመንገድ ሽፋን እና ዘመናዊነት እንዲሁም የትራንስፖርት ፍሰት ወደ ላቀ ደረጃ ሊያሳድግ የሚችል የመንገድ ኮሪደር እና የአካባቢ ልማቶች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

በዚህ መሠረት የሚለሙት የመንገድ ኮሪደሮች ይፋ የተደረጉ ሲሆን ከአራት ኪሎ በመስቀል አደባባይ እስከ ቦሌ ድልድይ 7 ኪሎ ሜትር፣ ከቦሌ አየር መንገድ እስከ መገናኛ ዳያስፖራ አደባባይ 4 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር መንገዶች በቀጣይ የሚለሙ መንገዶች ናቸው፡፡

በተጨማሪም ከመገናኛ ዳያስፖራ አደባባይ በአራት ኪሎ በኩል የአድዋ ድል መታሰቢያ አካባቢ ድረስ 6 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ከፒያሳ አድዋ ድል መታሰቢያ ዙርያ፣ በለገሃር – ሜክሲኮ – በሳርቤት እስከ ወሎሰፈር 10 ኪሎ ሜትር መንገድ በቀጠይ እንደሚሰራ ተመላክቷል፡፡

እነዚህ የመንገድ ኮሪደር ልማቶች ሁለንተናዊ የመንገድ ዘመናዊነት ያሟሉ ከመሆናቸውም በላይ ዓለም አቀፍ የስማርት ሲቲ ስታንዳርድን በማሟላት የከተማዋን ደረጃ ከፍ የሚደርጉ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቶቹ አዋሳኝ የወንዝ ተፋሰሶችን ያቀፉ፣ የብስክሌትና ሞተር አልባ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ፣ የከተማዋን ማስተር ፕላን እና ዲዛይንን ታሳቢ ያደረጉ እንዲሁም ለከተማዋ እጅግ ዘመናዊ የትራንስፖርት ፍሰት የሚያጎናፅፉ እንደሚሆኑ ታምኖባቸዋል።

በተጨማሪም አስፈላጊ በሆኑ የኮሪደሩ ቦታዎች ላይ ደረጃቸውን የጠበቁ ተሸጋጋሪ ድልድዮች፣ ማሳለጫዎች እና ሰፋፊ መጋቢ መንገዶችን ያቀፈ ሲሆን የከተማ አረንጓዴ ልማትን ያካተቱ እንደሚሆንኑም ተገልጿል።

የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔም የቀረበውን የመንገድ ኮሪደር ልማት እቅድ በጥልቀት መርምሮ በሙሉ ድምፅ ያፀደቀ ሲሆን ከነገው እለት ጀምሮ ወደ ስራ እንዲገባ መወሰኑን ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡