የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ በዓለም የንግድ ድርጅት የሚኒስትሮች ጉባዔ ላይ እየተሳተፈች ነው

By Melaku Gedif

February 26, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 13ኛው የዓለም የንግድ ድርጅት የሚኒስትሮች ጉባዔ ዛሬ በተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች አቡ ዳቢ መካሄድ ጀምሯል።

በድርጅቱ የታዛቢነት መቀመጫ ያላት ኢትዮጵያም በጉባዔው ላይ እየተሳተፈች ነው።

በጉባዔው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትርና የዓለም የንግድ ድርጅት ዋና ተደራዳሪ ገብረመስቀል ጫላ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋና የገንዘብ ሚኒስትር ዴዔታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ኢትዮጵያን ወክለው ተሳትፈዋል፡፡

”በንግድ ለሕዝብ መድረስ” በሚል መሪ ሃሳብ በሚካሄደው ጉባዔ ላይ የዓለም የንግድ ድርጅት የ164 አባል ሀገራት የንግድ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ አመራሮች መሳተፋቸው ተጠቁሟል፡፡

ጉባዔው የባለብዙ ወገን የንግድ ስርዓት፣ የዓለም የንግድ ድርጅት ተቋማዊ ማሻሻያ እንዲሁም የቀረጥና የታክስ ስርዓት ማሻሻያዎችና የምግብ ዋስትናን ጨምሮ ሌሎች ዓለምን እየፈተኑ ባሉ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክር ይጠበቃል።

ጉባዔው በጅማሮው የኮሞሮስና ቲሞር የአባልነት ጥያቄ ያጸደቀ ሲሆን÷ እስከ የካቲት 21 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚቆይ ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እየሰራች መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።