የሀገር ውስጥ ዜና

የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ሂደት ሁሉን አቀፍ እንዲሆን መንግስት ቁርጠኛ ነው – ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)

By Tamrat Bishaw

February 28, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ሂደት ሁሉን አቀፍ እንዲሆን መንግስት ቁርጠኛ እንደሆነ የፍትሕ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።

የፍትህ ሚኒስትሩ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በጄኔቫ በጀመረው 55ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ንግግር አድርገዋል።

ሚኒስትሩ በቪዲዮ በቀረበ ንግግራቸው፤ የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን በመግለጽ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ አቅርበዋል።

የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ሂደት ሁሉን አቀፍ፣ ተጎጂዎችን ያማከለ እና ግልጽነት ያለው እንዲሆን መንግስት ቁርጠኛ መሆኑንም አስረድተዋል።

እስካሁን የተደረገውን ቅድመ ዝግጅት በተመለከተ ባደረጉት ገለፃ፤ አጠቃላይ ሪፖርትና ረቂቅ ፖሊሲ በገለልተኛ የባለሙያዎች ቡድን ለፍትህ ሚኒስቴር መቅረቡን ተናግረዋል።

ረቂቁ በባለድርሻ አካላት ከተረጋገጠ በኋላም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ይቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።

የተመድ የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ጽህፈት ቤት በሂደቱ ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል።

በቀጣይም ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መንግስት ያለውን ቁርጠኝነት ማረጋገጣቸውን በጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል።