የሀገር ውስጥ ዜና

ሕንዳውያን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር 2ኛ ደረጃን ይይዛሉ – አቶ መላኩ አለበል

By Meseret Awoke

February 28, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ከ75 ሺህ ለሚበልጡ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል በመፍጠር ሕንዳውያን ሁለተኛ ደረጃን የያዙ የውጭ ባለሃብቶች ናቸው ሲሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አቅምና አማራጭ ለሕንድ ባለሀብቶች ለማስገንዘብ በሕንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ውይይት ተደርጓል፡፡

በመድረኩም የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ÷ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ማዕድን፣ አይሲቲና የቱሪዝም ዘርፎች በመንግስት ቅድሚያ የተሰጣቸው ዘርፎች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

በግብርና፣ ንግድ እና በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለሚሰማራ ባለሀብት አቅምን የሚጨምሩ ውጤታማና ትርፋማ የሚያደርጉ ወደር የለሽ የገበያ ተደራሽነት፣ የተትረፈረፈ የተፈጥሮ ሃብትና ውሃ እንዲሁም ለም መሬት መኖሩን ነው የገለጹት፡፡

በተጨማሪም የበለፀገ ማዕድን፣ የተለያዩ የኬሚካል ውጤቶች፣ ምቹና ተስማሚ የአየር ንብረት፣ አስተማማኝና ተመራጭ እንዲሁም በሁሉም ክፍለ ዓለም ተደራሽነት ያለው የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ስለመኖሩም አንስተዋል፡፡

አቶ መላኩ አክለውም ፥ መሠረተ ልማት የተሟላላቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የታክስ እፎይታና የተሳለጠ አሰራርን ጨምሮ የድጋፍ ጥቅልና ማበረታቻዎች ስለመኖራቸው ተናግረው ባለሃብቶች በተጠቀሱት ዘርፎች እንዲሰማሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ለኢንቨስትመንታቸው ስኬት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ መንግስት ያለውን ቁርጠኝነትም አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ ከ75 ሺህ ለሚበልጡ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል በመፍጠር ሕንዳውያን ሁለተኛ የውጭ ባለሃብት መሆናቸውን በመድረኩ አንስተዋል፡፡