የሀገር ውስጥ ዜና

በ6 ወራት ውስጥ ብቻ 1 ሺህ 358 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን አጥተዋል ተባለ

By Feven Bishaw

February 28, 2024

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት 1 ሺህ 358 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን አጥተዋል ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ተናገሩ፡፡

ሚኒስትር ዴኤታዋ በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው የትራፊክ አደጋን በተመለከተ ያነሱ ሲሆን ከሰሞኑ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢ የተከሰቱ አሳዛኝ የትራፊክ አደጋዎችን አንስተዋል፡፡

ሰሞኑን የተከሰተውን አደጋ ሳይጨምር በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ብቻ 1 ሺህ 358 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን ማጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በቁጥር ደረጃ በ514 የቀነሰ ቢሆንም የጉዳቱ ልክ አሁንም እጅግ አሳሳቢ መሆኑን መገንዘብ ይገባል ብለዋል፡፡

2 ሺህ 672 ሰዎች ደግሞ በመኪና አደጋ ሳቢያ ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው እና ከ1 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ውድመት መድረሱን ገልፀዋል፡፡

በሀገሪቱ የትራፊክ አደጋ መንስኤዎች ተብለው ከተጠኑ ዝርዝር ምክንያቶችም ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑ የትራፊክ አደጋዎች የሚደርሱት በአሽከርካሪዎች ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከ20 በመቶ የማያንሱት ደግሞ ከተሸከርካሪዎች ብቃት ማነስ ምክንያት የሚደርሱ መሆናቸውን ገልጸው፤ እነዚህ ሁለት ምክንያቶች ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

በዚህ ረገድ መንግስት የተለያዩ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት የመንገድ ደህንነት በትምህርት ስርዓት ውስጥ እንዲካተት መደረጉንና የአሽከርካሪ ብቃትን መመዘን እንዲሁም የተሸከርካሪ ደህንነት ምርመራ ማረጋገጥ ላይ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

የትራፊክ አደጋዎችን ለመቀነስ የትራፊክ ህግን አክብሮ ማሽከርከር፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለንን አመለካከት መቀየር እንደሚያስፈልግ አሁን ቆም ብለን የምናስብበት ወቅት ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

የትራፊክ አደጋዎችን ለመቀነስ ከፍተኛ ሀላፊነት ያለባቸው ሚዲያዎች የሁልጊዜ አጀንዳቸው አድርገው ሊሰሩ እንደሚገባ ሚኒስትር ዴዔታዋ አስገንዝበዋል።

በፌቨን ቢሻው