የሀገር ውስጥ ዜና

የአውሮፓ ህብረት ለብሄራዊ ዲሞቢላይዜሽንና መልሶ ማቋቋም ፕሮግራም ማስፈፀሚያ 16 ሚሊየን ዩሮ ለገሰ

By Melaku Gedif

March 01, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረት ለብሄራዊ ዲሞቢላይዜሽንና መልሶ ማቋቋም ፕሮግራም ማስፈፀሚያ 16 ሚሊየን ዩሮ ለገሰ።

በገንዘብ ሚኒስቴር በተከናወነው የፊርማ ስነ-ስርዓት አምባሳደር ተሾመ ቶጋ የብሄራዊ ተሀድሶ ኮሚሽነርን ጨምሮ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው፣ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሚስተር ሮናልድ ኮቢ፣ የተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ ተጠሪ ዶክተር ራሚዝ አላብባራብ እና የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም የኢትዮጵያ ተጠሪ ዶክተር ሳሙኤል ዶ ተገኝተዋል።

የገንዘብ ድጋፉ የብሄራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን በበላይነት ለሚመራው እና በሰላም ስምምነት መሰረት ትጥቃቸውን አስረክበው በሰላማዊ መንገድ ህይወታቸውን ለመምራት የፈቀዱ የቀድሞ ተዋጊዎችን ዲሞቢላይዝ ለማድረግና በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም ለተነደፈው ፕሮግራም ማስፈፀሚያ የሚውል መሆኑ ተገልጿል።

አምባሳደር ተሾመ ድጋፉ ለፕሮግራሙ የመጀመሪያው በር ከፋች እርምጃ በመሆኑ አመስግነው፤ የዚህ ዓይነቱ ድጋፍ በህብረቱ እና በአባል ሀገራቱ ጭምር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የዲሞቢላይዜሽንና መልሶ ማቋቋም ፕሮግራም ስኬት ለኢትዮጵያ ብሎም ለቀጣናው የሰላም ግንባታ ቁልፍ ሚና ያለው በመሆኑ ሁሉም የልማት አጋሮችና የሰላም ወዳጆች የአውሮፓ ህብረትን ፈለግ በመከተል ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።