የሀገር ውስጥ ዜና

የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት በተግባር የተገለጠበት ድል ነው- ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን

By Feven Bishaw

March 01, 2024

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን የሚታወቁበት ኅብረ ብሔራዊ አንድነት በተግባር የተገለጠበት ድል መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ።

ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ የ128ኛው የዓድዋ ድል በዓልን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸው÷ኢትዮጵያውያን እጅግ አኩሪ ድሎችና ታሪኮች ያሏቸው ህዝቦች ናቸው ያሉ ሲሆን ÷ቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን ለሀገራቸው ያለስስት ራሳቸውን መስጠታቸውንም አንስተዋል።

የዓድዋ ድል ሲነሳ ከሁሉም የሚያስደንቀው ኢትዮጵያውያን በጉልህ የሚታወቁበት አንድነት በተግባር የተገለጠበት ድል መሆኑንም አቶ አሻድሊ ተናግረዋል።

የአሁኑ ትውልድም ለሀገር ሉዓላዊነት ሲባል ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ድል የገለጡትን እውነተኛ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት በአግባቡ መረዳትና መጠቀም ይኖርበታል ብለዋል።

እንዲሁም “ሀገራችን አሁን የጀመረቻቸው አስደናቂ ስኬቶቿን ለማስቀጠል፣ ለቀጣዩ ትውልድም የተሻለች ሀገር ለማስረከብ ሁላችንም ኃላፊነታችንን መወጣት ይጠበቅብናል” ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።