የሀገር ውስጥ ዜና

አቶ አረጋ ዓድዋን ስናከበር ፈተናዎችን በድል ለመሻገር ራሳችንን በማዘጋጀት ሊሆን ይገባል አሉ

By Mikias Ayele

March 02, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓድዋን ስናከበር የገጠሙንን ወቅታዊ ፈተናዎች በድል ለመሻገር ራሳችንን በማዘጋጀት ሊሆን እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አስገነዘቡ፡፡

ርዕሰ መሥተዳደሩ 128ኛውን የዓድዋ ድል በዓል አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም÷ የዓድዋ ድል የኅብር ማሳያ፣ በአባቶቻችንና እናቶቻችን ተጋድሎና አይበገሬነት የተገነባ፣ የጀግንነት ዓርማ፣ የሀገር ፍቅር እና የሰንደቅዓላማ ክብር ምንነት መገለጫ ነው ብለዋል፡፡

ይህን ታላቅ የድል በዓል ስናስብም ኢትዮጵያን ጠብቀው ያቆዩ አባቶቻችንና እናቶቻችንን ከማሰብ ባሻገር÷ እንደነሱ የገጠሙንን አሁናዊ ፈተናዎች በድል ለመሻገር በመዘጋጀት ሊሆን ይገባል ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪ በኅብር፣ በቁርጠኝነትና አይበገሬነት ለመሥራትና የራሳችንን ደማቅ ታሪክ ለመፃፍ በመዘጋጀት እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት፡፡