የሀገር ውስጥ ዜና

ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በጋራ ለመስራት ተስማሙ

By Feven Bishaw

March 02, 2024

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በጋራ ለመስራት የእህትማማች ከተሞች ስምምነት ተፈራርመዋል::

ሁለቱ ከተሞች በቀጣይ በሰው ተኮር ፣ በአቅም ግንባታ ፣ በልምድ ልውውጥ እንዲሁም በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ላይ በጋራ ለመስራት የተግባቡ ሲሆን÷ ስምምነቱን የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች ተፈራርመዋል::

በዚህ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ÷የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ልምድና ተሞክሮዎቹን ለማካፈል ዝግጁ መሆኑን ገልፀው ልበ ቀና ባለሃብቶችን በማስተባበር ለድሬዳዋ ከተማ የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከልን ለመገንባት ቃል መግባታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ፅህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።

የድሬዳዋ ከንቲባ ከድር ጁሀር ÷አዲስ አበባ ከሀገራችን አልፎ ለዓለም ከተሞች ልምድ የምታካፍል ከተማ መሆኗን ገልፀው ይህንን የዳበረና ስኬታማ ተሞክሮ ወስደን በከተማችን ተጨባጭ ሁኔታዎች ላይ ተግባራዊ እናደርጋለን ብለዋል::