አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደብረብርሃን ከተማ ከ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ አራት ፋብሪካዎች ተመርቀዋል።
የደብረብርሃን ከተማ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሀላፊ አቶ ብርሃን ገብረህይወት÷ በ10 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ወጪ የተገነቡ 17 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በዚህ ዓመት ማምረት መጀመራቸውን ገልጸዋል።
ከእነዚህ መካከል አራቱ አምራች ኢንዱስትሪዎች የፌደራል እና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች በተገኙበት ዛሬ ተመርቀዋል፡፡
ኤም ዲ ኤፍ ማምረቻ፣ ጅንሹ ኢትዮጵያ ቴክስታይል ቴክኖሎጂ፣ ሊሐም የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ እና ሒንዲ የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ ፋብሪካዎች ናቸው ዛሬ የተመረቁት።
የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹ ከ3 ሺህ በላይ የስራ እድል እንደፈጠሩም አብራርተዋል።
በከተማው እስካሁን ከ115 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 621 ኢንዱስትሪዎች መኖራቸው የተገለጸ ሲሆን÷ ከእነዚህ መካከል 98ቱ በማምረት ላይ የሚገኙ ናቸው ተብሏል፡፡
በምረቃ መርሐ ግብሩ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን፣ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ሃላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
በግርማ ነሲቡ