የሀገር ውስጥ ዜና

ለሕዳሴ ግድቡ እስካሁን 18 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር መሰብሰቡ ተገለጸ

By Melaku Gedif

March 06, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እስካሁን 18 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ከሕዝብ ተሳትፎ መሰብሰቡን የሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍቅርተ ታምር በሰጡት መግለጫ÷ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁሉም ኢትዮጵያዊ መግባባት ላይ የደረሰበት የከፍታችን ምልክት ነው ብለዋል።

የመሠረት ድንጋይ የተጣለበትን 13ኛ ዓመት “በኅብረት ችለናል” በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ገልፀዋል።

ባለፉት 13 ዓመታት እስካሁን 18 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ከሕዝብ ተሳትፎ መሰብሰቡን ነው የተናገሩት፡፡

የመንግሥት ቁርጠኛ አቋምና የዲፕሎማሲ ጥረት እንዲሁም የመላው ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ውጤት መሆኑን ገልፀዋል።

የይቻላል መንፈስ የፈነጠቀ ታላቅ ፕሮጀክት መሆኑን ገልፀው÷ በቀጣይም መሰል ፕሮጀክቶችን በተባበረ ክንድ መፈፀም ይገባናል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በ13ኛው ዓመት ክብረ-በዓል የቦንድ ሳምንት፣ አውደ-ርዕዮች፣ የምስጋና፣ ዕውቅናና ሌሎች የድጋፍ ማሰባሰብ የንቅናቄ መድረክ ዝግጅቶች እንደሚደረጉ ገልፀዋል።

በንቅናቄ ዝግጅቶችም 300 ሚሊየን ብር ለማሰባሰብ መታቀዱን ጠቁመው÷ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።