አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጋር የኮርት ሲስተምን ማዘመን የሚስያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።
በስምምነቱ ወቅት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት÷ በፍርድ ቤቶች የሚሰሩ ስራዎች ከሌሎች ተቋማት ጋር ከፍተኛ ትስስር ያላቸው በመሆኑ በቴክኖሎጂ ራሳቸውን ማዘመን ከጊዜው ጋር አብሮ ለመጓዝ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
ተቋማቸው ከኢመደአ ጋር ሲሰራ እንደነበር አስታውሰው÷ የዛሬው ስምምነትም ሌላ ምዕራፍ መሆኑን አንስተዋል።
በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሚተገበረው የዲጂታል ኮርት ሲስተም ከሁለት አመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ እውን መሆን እንደሚገባው በመግለጽ ክትትልና ድጋፍም ይደረጋል ነው ያሉት፡፡
የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ በበኩላቸው÷ የፍርድ ቤት ስራዎች ጥንቃቄ የሚጠይቁ እንደሆነ በማንሳት የተሻለ የኮርት ስርዓት ለመተግበር ቁርጠኛ ነን ብለዋል፡፡
በፕሮጀክቱ የደህንነት ደረጃቸው የላቁ የኮሙዩኒኬሽን መሳሪያዎች ከመተግበር ባሻገር እንደ “ፒኬአይና” ብሄራዊ መታወቂያን አቀናጅተን እንተገብራለን ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የሚተገበረው ስርዓት ሰነዶችን ዲጂታል በማድረግ ግልፅና ተጠያቂነት ያለው የዳኝነት ስርዓት በመፍጠር ለፍርድ ቤቶች መፍትሄ ከመስጠቱም በላይ ውጤታማ ስራ እንዲያከናውኑ አስተዋፆ እንደሚያበረክት ከአስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡