የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያና አንጎላ ነባሩን የአየር አገልግሎት ስምምነት በአዲስ አሻሽለው ተፈራረሙ

By Melaku Gedif

March 08, 2024

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና አንጎላ ነባሩን የአየር አገልግሎት ስምምነት በአዲስ መልክ አሻሽለው ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግስቴ እና የአንጎላ ብሔራዊ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የቦርድ ሰብሳቢ አሜሊያ ዶሚኒጌስ ኩቪንጉዋ ተፈራርመዋል፡፡

በሁለቱ ሀገራት መካከል ከ47 ዓመታት በፊት ተፈርሞ የነበረውን የአየር አገልግሎት ስምምነት በአፍሪካ የአየር ክልል ላይ ያለምንም ገደብ የበረራ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡

በስምምነቱ መሰረት በሚወከሉ አየር መንገዶች ቁጥር፣ በበረራ ምልልስ፣ የአይሮፕላን አይነት እና የመዳረሻ ነጥቦች ላይ ገደብ የሌለው፣ በአዲስ አበባና በአንጐላ መካከል በ3ኛ እና 4ኛ በአፍሪካ ውስጥ ደግሞ በሙሉ 5ኛ ትራፊክ መብት መብረር እንደሚቻል ተገልጿል፡፡

ተወካይ አየር መንገዶችን እርስ በራሳቸውና ከሦስተኛ ወገን ጋር በሽርክና ሊያሠራ የሚችል እና ከተደራራቢ ቀረጥ ነፃ የሚያደርግ የአየር አገልግሎት ስምምነት መፈረሙንም የሲቪል አቪዬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡