የሀገር ውስጥ ዜና

የሴቶች የተሃድሶና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ተካሄደ

By Feven Bishaw

March 14, 2024

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢሲ )ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በ100 ሺህ ካሬ ሜትር ስፍራ ላይ ያረፈው የሴቶች የተሃድሶና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ምረቃ-ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል፡፡

ማዕከሉ በዋነኛነት በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶችን በመቀበል ሙያዊ እና ስነ ልቦናዊ ድጋፍ፣ ክትትልና ስልጠናዎችን እንዲያገኙ በማድረግ ወደ ሥራ እንዲሰማሩ የሚያስችል መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በአንድ ዙር ብቻም 10 ሺህ ሴቶችን ተቀብሎ የማሰልጠን አቅም ያለው መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

ወጣት ሴቶቹ በማዕከሉ ቆይታቸው ከሚያገኙት የስነ ልቦና ድጋፍ በተጨማሪ በስነ-ውበት፣ በከተማ ግብርና ፣ በምግብ ዝግጅት፣ በከተማ ውበት አጠባበቅና በኮምፒዩተር ሙያ ስልጠና በመውሰድ ወደ ስራ እንዲገቡ ይደረጋል ተብሏል፡፡

በተጨማሪም በሞግዚትነት፣ በመስተንግዶ፣ በፀጉር ሥራ፣ በኤሌክትሪክና ሸክላ ስራ፣ በእንጨት ስራዎች፣ በልብስ ስፌት እንዲሁም በሌሎች የሙያ ዘርፎች በቂ ስልጠና በመስጠት ወደ ስራ እንዲገቡ እንደሚደረግ ተጠቅሷል፡፡

ማዕከሉ በውስጡ የተሃድሶ ሥልጠና የሚሰጥባቸው የክህሎት ማበልፀጊያ፣ የማሰልጠኛ ማዕከላት፣ የሥነ-ልቦና እና ምክር አገልግሎት እንዳሉት ተገልጿል፡፡

ከዚህ ባለፈም የሕክምና ማዕከል፣ ዶርሚተሪ፣ መመገቢያ አዳራሾች እንዲሁም የስፖርት ማዘውተሪያ እና የመዝናኛ ስፍራዎች እንደሚይዝ ነው የተጠቆመው፡፡

በህይወት አበበ እና ዘቢብ ተክላይ