የሀገር ውስጥ ዜና

ለኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ተበረከተ

By Tamrat Bishaw

March 15, 2024

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ዶክሜንቶች ጨምሮ የተለያዩ ታሪካዊ፣ ባህላዊ ቅርሶችና መዛግብት ተበረከቱለት፡፡

ቅርሶቹንና መዛግብቱን ያበረከቱት በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ሰዎች ሲሆኑ÷ ሥጦታውንም ለተቋሙ ዳይሬክተር ታከለ መርዕድ (ዶ/ር) አስረክበዋል።

ከቅርሶቹ መካከልም ጀርመን ሀገር ከሚገኙ ቤተሰቦች የተበረከተ ከ1 ሺህ 300 በላይ ፎቶግራፎችን የያዙ ሦስት ዘመን ተሻጋሪ የፎቶ አልበሞች ይገኙበታል።

አልበሞቹም በጀርመን የፎቶግራፍ ባለሙያዎች ከፈረንጆቹ 1883 እስከ 1946 በኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ የተቀረፁ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን÷ የተለያዩ ኩነቶችንና ቦታዎችን የሚያሳዩ መሆናቸውም ተጠቅሷል፡፡

ከሀገር ውስጥ ግለሰቦች ከተበረከቱት መካከልም÷ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ዶክሜንቶች ጨምሮ ጥንታዊ የመገበያያ ሳንቲሞች፣ ከ3 መቶ በላይ መጽሐፍት፣ ፎቶ ግራፎች፣ ፊልሞችና ሌሎች ቁሶች ይገኙበታል፡፡

ተቋሙ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህልና ብዝኃ- ማንነት ይዘት ያላቸውን ጉዳዮች በጥናትና ምርምር በታገዘ መልኩ ተደራሽ በማድረግ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡

በሳሙኤል ወርቃየሁ