አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል 73 የመስኖ የግድብ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ እንዳሉት ፥ መንግስት ላለፉት አራት ዓመታት የክልሉን ግብርና ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ የሚረዱ ኢኒሼቲቮችን በማስፋፋት ላይ ነው፡፡
ከእነዚህም አንዱ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ሲሆን ፥ እስካሁን መጠናቀቅ ጨምሮ፣ በተለያዩ የግንባታ ደረጃዎች ላይ የሚገኙ 73 የግድብ ፕሮጀክቶችን እያከናወነ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የፌዴራል መንግስት በክልሉ እየገነባቸው የሚገኙ የመስኖ ውሃ ግድብ ፕሮጀክቶችንም በቅርበት በመከታተል ላይ እንደሚገኝ ነው የጠቆሙት።
ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል በምስራቅ ባሌ ዞን ውስጥ በመሰራት ላይ የሚገኘውን የጨልጨል የመስኖ ልማት ፕሮጀክት እና በባሌ ዞን ውስጥ በመሰራት ላይ የሚገኘውን የወልመል የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ጠቅሰዋል፡፡
የወልመል መስኖ ልማት ፕሮጀክት – በባሌ ዞን ሀረና-ቡልቅ እና ደሎ መና ወረዳ የሚገኝ ሲሆን ፥ሲጠናቀቅ 11 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ያለማል ተብሏል፡፡
ስራው በሁለት ሎቶች ተከፍሎ በመከናወን ላይ የሚገኝ እንደሆነ የገለጹት አቶ ሽመልስ ፥ ሎት-1 የወንዝ መቀልበሻና ዋና ቦይ ስራዎችን ያካትታል ብለዋል፡፡
ሎት-2 ደግሞ የመስኖ መሬት ዝግጅት ሥራን የሚያካትት ሲሆን ፥ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ 66 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የጨልጨል መስኖ ልማት ፕሮጀክት ፥ በምስራቅ ባሌ ዞን ራይቱ ወረዳ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ፥ ግንባታው ሲጠናቀቅ 4 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ የማልማት አቅም እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡
መንግስት እነዚህ ፕሮጀክቶች የክልሉ ኢኮኖሚ ሃይል ከመሆን አልፈው ፥የኢትዮጵያ የግብርና ሽግግር የሚያፋጥኑ መሆናቸውን በማመን፣ በተያዘላቸው ፍጥነትና ጥራት እንዲከናወኑ ያላሰለሰ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ላይ ያለ ሲሆን ፥ በቀጣይ አጠንክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡
በተጨማሪም በእነዚህ ዞኖች በክልሉ መንግስት ወጪ እየተገነቡ ያሉ የፊና የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች ያሉ ሲሆን ፥ እነሱም፣ በምስራቅ ባሌ ዞን (አራት)፡ ዶፋ፣ ካታ ድቤ፣ ጎይዴር እና ባኬ ሃሮ እንዲሁም በባሌ ዞን ፡ (አንድ) ያዶት ናቸው ብለዋል፡፡