የሀገር ውስጥ ዜና

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከፋሪስ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ጋር በትብብር ለመሥራት ተፈራረመ

By ዮሐንስ ደርበው

March 19, 2024

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ፋሪስ ቴክኖሎጂ ግሩፕ በምርምርና ፈጠራ ሥራ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

ስምምነትቱን የፈረሙት የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) እና የፋሪስ ቴክኖሎጂ ግሩፕ መስራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኤልያስ ይርዳው ናቸው።

ሳሙኤል (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንዳሉት÷ ዩኒቨርሲቲው የአምስት ዓመቱን ስትራቴጂ ለማሳካት ከያዛቸው ግቦች መካከል ሀገራዊ ፋይዳ ካላቸው የግል ዘርፎች ጋር በትብብር መሥራት አንዱ ነው።

ከፋሪስ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ጋር የተደረገው ስምምነትም የስትራቴጂው አካል መሆኑን ጠቅሰው÷ በጥናትና ምርምር እንዲሁም ፈጠራ ላይ በትብብር ይሠራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የተማሪዎችን የፈጠራ ሐሳብ ወደ ሀብት ለመለወጥ በሚደረገው ጥረትም የስምምነቱ ፋይዳ የጎላ ነው ብለዋል፡፡

ኤሊያስ ይርዳው በበኩላቸው÷ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያለውን እምቅ አቅም ለመጠቀም ስምምነቱ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል።

ግሩፑ ቴክኖሎጂ ነክ የሆኑ በርካታ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየሠራ መሆኑን በመግለጽ ስምምነቱ የፕሮጀክቶችን ውጤታማነት ይበልጥ እንደሚያሳድገው አመላክተዋል፡፡