አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የአፈር ማዳበሪያ ዕዳ ለመሰብሰብ እና ህገ ወጥ ስርጭትን ለመከላከል የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው ገለፁ፡፡
በክልሉ የዞኖች እና የልዩ ወረዳዎች የሠላምና ፀጥታ አዝማሚያ፣ የግብርና ልማት ዕቅድ አፈጻጸም እና የገቢ አሰባሰብ ሁኔታን የሚገመግም መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ አቶ እንዳሻዉ ጣሰው እንዳስገነዘቡት÷ ክልሉ በዕቅዱ መሰረት እየሄደ ቢሆንም የመዋቅሮችና የሴክተሮች አፈጻጸም ልዩነት ያለው በመሆኑ ሊታረም ይገባል።
ከሠላምና ፀጥታ አኳያ የተደረጉት ጥረቶችና የተገኙት ዉጤቶች አበረታች መሆናቸውን ጠቅሰው÷ በቀጣይ በየአካባቢው ችግር የሚያባብሱ ጉዳዮችን ለይቶ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ከግብርና ልማት አንፃር ወቅታዊና መደበኛ የግብርና ልማት ተግባራትን በማጠናከር ምርታማነትን ለማሳደግ አጋዥ የሆኑ አሠራሮችን፣ ቴክኖሎጂዎችንና ግብዓቶችን የማሟላት ተግባር በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባዉ ተናግረዋል።
ምርታማነትን ለማሳደግ ጥረት ከማድረግ ጎን ለጎን የገበያ ትስስር ስርዓትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ከአፈር ማዳበሪያ ዕዳ አሰባሰብና ከህገ ወጥ ስርጭት አንፃር የተጀመረው ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
ከክልሉ ተነፃፃሪ ጥቅምና አጠቃላይ ሁኔታ አንፃር የአበባ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማትን ለማጠናከር በተጠናና በታቀደ መንገድ በቀጣይ በትኩረት እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
ከገቢ አሰባስብ አኳያ እያንዳንዱ መዋቅር በዕቅዱ መሠረት የተደራጀ ንቅናቄ በማድረግ ዉጤታማ ሥራ እንዲሠራ አቅጣጫ መቀመጡን የክልሉ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።