አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ የአባላት ኮንፈረንስ “ቃልን በተግባር ለኢትዮጵያ ብልጽግና “በሚል መሪ ሃሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ጀምሯል፡፡
በኮንፈረንሱ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፣ በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ/ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ፣ የአዲስ አበባ ም/ቤት አፈጉባዔ ወ/ሮ ቡዜና አልከድርን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
የአባላት ኮንፈረንሱ የብልጽግና ፓርቲ የግማሽ ምርጫ ዘመን አፈፃፀም የሚገመገምበት እና የቀጣይ አቅጣጫዎች የጋራ የሚሆኑበት መሆኑ ተገልጿል፡፡
ፓርቲው ለብዝሃ ቋንቋ በሰጠው ትኩረት ከአማረኛ በተጨማሪ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛ እና አፋርኛ የፌደራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በአምስቱም ቋንቋዎች ፕሮግራሙ እየተዋወቀ ይገኛል፡፡
በመድረኩ የሁሉም ክልሎች ተወካዮች በየቋንቋዎቻቸው መልዕክቶቻቸውን ማስተላለፋቸውንም የከተማዋ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ÷ፓርቲው፣ በባለፉት ሁለት ተኩል የምርጫ ዘመን አጋማሽ ዓመታት አባላቱን እና አመራሩን አቀናጅቶ በመምራቱና ሕዝቡን በቀጥታ በማሳተፉ አበራታች ውጤቶች አስመዝግቧል ብለዋል ።
የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ በምርጫ ዘመን አጋማሽ በአፈፃፀሞቻችን የተገኙ ስኬቶችንና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ቆም ብሎ መመዘንና መፈተሸ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በባለፉ ሁለት ተኩል ዓመታት አንፀባራቂ ድሎችን ስናስመዘግበ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ አልነበረም ሲሉም ገልጸዋል።
በርካታ ፈታኝ ሁኔታዎች ገጥመውናል፤ መሻገር የቻልነው በያዝነው የፖለቲካ ዓላማ ጽናት በመርህ ላይ ቆመን በመታገላችን ነው፤ ፈተናውን መቋቋም ያልቻሉ ከረጅሙ የትግል ጉዞ ገና በማለዳው ተለይተውናል ብለዋል።