አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከአሸከርካሪዎች ጋር በመመሳጠር ተገልጋዩን ለእንግልት የዳረጉ ከ350 በላይ የስምሪት ተቆጣጣሪዎችና የዘርፉ የሥራ ሃላፊዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የኦሮሚያ ትራንስፖርት ኤጀንሲ አስታወቀ።
የኤጀንሲው ሃላፊ አቶ ዳንኤል ቸርነት እንደገለፁት÷ በክልሉ የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ሆነው ከመስመራቸው በሚጠፉና ተሳፋሪውን በሚያንገላቱ 2 ሺህ 800 ተሽከርካሪዎች ላይም እርምጃ ተወስዷል።
በተለይም ከመስመር በሚጠፉና ተሽከርካሪ በሚደብቁ ላይ በተወሰደ ህጋዊና አስተማሪ እርምጃ ከ17 ሚሊየን ብር በላይ ለመንግሥት ገቢ ተደርጓል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የነዳጅ ድጎማን ከማቋረጥ ጀምሮ የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዱን ነው የጠቆሙት።
በኤጀንሲው የትራፊክ ደህንነት ማረጋገጫ ዳይሬክተር አቶ ዓለሙ ለማ በበኩላቸው÷ በትራንስፖርት መናኸሪያዎችና በስምሪት ላይ ተገልጋዩን ህብረተሰብ ለእንግልት የዳረጉ ችግሮች አሉ ብለዋል።
ኤጀንሲው በሸገር ከተማ አስተዳደር አምስቱ መግቢያና መውጫ በሮችን ጨምሮ በክልሉ ሁሉም ዞኖች ጠንካራ ቁጥጥር እያደረገ እንደሆነ መጥቀሳቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በክልሉ የትራንስፖርት ዘርፍ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በተወሰደው እርምጃ በተለይም ከክልሉ ዞኖችና ዋና ዋና ከተሞች ወደ ወረዳዎች በተቀመጠው ታሪፍ መሰረት የሚጭኑ ቢሆንም ከወረዳዎች ሲመለሱ ከወንበርና ከታሪፍ በላይ ያስከፍላሉ ብለዋል።
ኤጀንሲው ባለፉት ስምንት ወራት ከቢሮ ጀምሮ እስከ መናኸሪያ ድረስ ከአሽከርካሪዎች ጋር በመመሳጠር በምዝበራ፣ ብልሹ አሰራርና ህገ ወጥ ተግባር የተሳተፉ ከ350 በላይ በሚሆኑት ስምሪት ተቆጣጣሪዎችና የሥራ ሃላፊዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።
በዚህም ከማስጠንቀቂያ ጀምሮ በደሞዝ መቀጮና ከቦታ የማንሳት እርምጃ ወስደናል ብለዋል።