አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በቱሪዝም ዘርፍ የተከናወኑ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ክልሉን ከማስተዋወቅ ባለፈ ኢኮኖሚውን እያነቃቁ እንደሆነ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እንደተናገሩት፤ በክልሉ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን በማልማት ክልሉን የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በተሰሩ ሥራዎች ውጤት ተመዝግቧል።
ለቱሪዝም ምቹ የሆኑና የጎብኚዎችን ቀልብ የሚስቡ በርካታ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ እና ባህላዊ ሀብቶች በክልሉ ቢኖሩም ባለፉት ጊዜያት ትኩረት ሳይሰጣቸው መቆየቱን አስታውሰዋል።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ያሉትን የቱሪዝም ሀብቶች ለማልማት የፌዴራልና የክልል መንግስታት ተቀናጅተው በአዲስ ዕይታ የፈፀሟቸው ተግባራት ስኬታማ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት የተከናወኑ እንደ ሀላላ ኬላ እና ጨበራ ጩርጩራ ያሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ክልሉን ከማስተዋወቅ ባለፈ ኢኮኖሚውን በማነቃቃትና የሥራ ዕድል በመፍጠር ጉልህ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህን ተከትሎ የክልሉ መንግስትና የዞን መዋቅሮች የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት ለጎብኚዎች ክፍት ለማድረግ እያከናወኑት ያለው ተግባር ዘርፉን እያነቃቃው ይገኛል ሲሉም ገልጸዋል።
ባለሀብቶችም በክልሉ ሆቴልና አገልግሎትን ጨምሮ በተለያዩ የልማት ዘርፎች እንዲሰማሩ ጥሪ ያቀረቡት ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር)፤ ለዚህም ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የክልሉን ዝግጁነት እንዳረጋገጡ ኢዜአ ዘግቧል።