አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 1 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ ከሩሲያ አምባሳደር ኢቭጄኒይ ተረክህን ጋር ተወያይተዋል።
አቶ ገዱ አትዮጵያ እና ሩሲያ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪካዊና በወዳጅነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዳላቸው በመግለጽ፥ ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።
ሩሲያ ከአራት ቀናት በፊት ግንቦት 27 ቀን 2012 ዓ.ም ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቷ በኩል የሰጠችው መግለጫ ሃገሪቱ ለዓለም አቀፍ መርህ መከበር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው በማለት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በሰጠችው መግለጫ ሩሲያ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለችው መሆኑንና በሶስቱ ሃገራት መካከል የሚደረጉ ውይይቶች የሁሉንም የተፋሰሱ ሃገራት የጸጥታና በውሃው በመጠቀም የመልማት መብት ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ መሆን አለበት ብላ እንደምታምን መግለጿ ይታወቃል።
በተጨማሪም ሶስቱ ሃገራት ልዩነታቸውን በፈረንጆቹ 2015 በደረሱት የመርሆዎች መግለጫ ስምምነት መሰረት በውይይት እንዲፈቱ ማሳሰቧም የሚታወስ ነው።
አቶ ገዱ ሩሲያ የኮቪድ ወረርሽኝን ለመከላከል እያደረገች ያለውን ጥረትም አድንቀው፥ ኢትዮጵያ ኮቪድን ለመከላከል ከሩሲያ እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥልም ገልጸዋል።
አምባሳደር ኢቭጄኒይ ተረክህን በበኩላቸው ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ግንኙነት ልዩ ዋጋና ትኩረት እንደምትሰጥ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ያላቸውን ልዩነት በውይይት እንዲፈቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ናት ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።