አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገርን በፅኑ መሰረት በማኖር የጋራ ትርክት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የታላቁ ህዳሴ ግድብን የስኬት ምንጮች በማሳያነት መጠቀም እንደሚገባ ርዕሳነ-መሥተዳደሮች አመላከቱ፡፡
በግድቡ ላይ የታየውን አንድነት ሌሎች ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሠራ ባለው ሥራ ላይ መተግበር እንደሚያስፈልግ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አሻድሊ ሀሰን አስገንዝበዋል፡፡
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው÷ በፈተናዎች የፀናው ታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሀገራችን ለያዘችው ሀገራዊ ምክክር ምሳሌ ሆኖ እንደሚያገለግል አመላክተዋል፡፡
ርዕሳነ-መሥተዳድሮቹ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ የግድቡ ስኬት ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ችግር ውስጥ ቢሆኑ በሀገራቸው ጉዳይ ያላቸው አቋም ተመሳሳይ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ግድቡ በችግሮች ውስጥም÷ ስኬት፣ ድልና ሀገራዊ አንድነት እንደሚመዘገብ ማረጋገጫ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡
በመሆኑም አሁን ላይ ሀገርን በፅኑ መሰረት በማኖር የጋራ ትርክት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የታላቁ የኢትዮጵያን የህዳሴ ግድብ የስኬት ምንጮችን መጠቀም እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
በሰሎሞን ይታየው