የሀገር ውስጥ ዜና

በአቶ አሻድሊ ሃሰን የተመራ ልዑክ የተለያዩ የግብርና ልማት ሥራዎችን ጎበኘ

By Melaku Gedif

March 31, 2024

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን የተመራ ልዑክ በሆሞሻና ኡራ ወረዳዎች የግብርና ልማት ሥራዎችን ጎብኝቷል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በጉብኝታቸው በሆሞሻ ወረዳ ጉሙ ቀበሌ በአነስተኛ መሬት ላይ የተጀመረውን የአቮካዶ ምርት ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡

አቶ አሻድሊ ÷ በሆሞሻ ወረዳ በሁለት ሔክታር የተጀመረው የተሻሻለ አቮካዶ ችግኝና ምርት በሁሉም ወረዳዎች በክላስተር ማስፋት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በተጨማሪም በኡራ ወረዳ በአርኤልኤልፒ ፕሮጀክትና በህብረተሰብ ተሳትፎ እየተሰራ ያለውን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ጎብኝተዋል፡፡

ልዑካኑ በአምባ 11 ችግኝ ጣቢያ እና በአምባ አንድ 50 ሔክታር መደበኛ መስኖ ልማት እንቅስቃሴን እንደጎበኙም የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡

በጉብኝቱ አቶ አሻድሊ ሃሰንን ጨምሮ የክልሉ ብልጽግና ፖርቲ ቅ/ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ኢሳቅ አብዱልቃድር፣ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበክር ኸሊፋ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።