የሀገር ውስጥ ዜና

የሥራና ክኅሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ከኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ጋር ተወያዩ

By ዮሐንስ ደርበው

April 01, 2024

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሥራ ክኅሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ከኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ጋር እንደ ተቋም በጋራ በሚሠሩ ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ገለጹ፡፡

ሚኒስትሯ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ በዘርፋችን ርብርብና ልዩ ትኩረት በሚጠይቁ ጉዳዮች ላይ ውጤታማ ውይይት አካሂደናል ብለዋል፡፡

ውይይታችን ከዚህ ቀደም በክኅሎት ልማት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና እና ሰላማዊ ኢንዱስትሪ ግንኙነትን ከማስፈን አኳያ የተግባባንባቸውን ጉዳዮች ይበልጥ ለማላቅና የተቀመጡ ሀገራዊ ግቦቻችንን በማሳካት የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለመ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በዚህም ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የተያዘውን ግብ ለማሳካት በቅንጅት የመሥራት ጅማሯችንን ማስፋት እንደሚገባን ተግባብተናል ነው ያሉት ሚኒስትሯ፡፡

ከውይይቱ ባለፈም በኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ተኪ ምርቶች ላይ ሀገራዊ አቅም ለመፍጠር የተጀመሩ ሥራዎችን መመልከታቸውን በመጥቀስ÷ ይህም ከቴክኖሎጂ አኳያ እንደ ሀገር ተስፋ ሰጪና የሁሉንም ድጋፍና ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን ተገንዝበናል ብለዋል፡፡

ርዕሰ መሥተዳድር ሽመልስ በክኅሎት ልማት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በሰላማዊ ኢንዱስትሪ ግንኙነት ላይ መሥራት ከሀገራዊ ግቦች ስኬት በላይ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ጉዳይ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት በቅንጅት አብሮ ለመሥራት ላሳዩን ቁርጠኝነት እና እየሰጡ ላሉት ቁርጠኛ አመራር ምስጋና አቅርበዋል፡፡