አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኅብረት ሥራ ማኅበራት የሀገር ኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ልማትን የማፋጠን ሚናቸው የጎላ ነው ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ፡፡
የክልሉ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ሪፎርም ንቅናቄ ይፋዊ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሂዷል።
አቶ አረጋ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የኀብረት ሥራ ማኅበራት በተለያዩ የዓለም ሀገራት ልማትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እና የልማት ማነቆዎችን በመፍታት መተኪያ የሌላቸው ተቋሞች ናቸው።
የኢኮኖሚ ቀውስን በመቅረፍ ሚናቸው ከፍተኛ እንደሆነ ጠቁመው÷ ዴሞክራሲያዊ አሠራር በተግባር የሚገለጽባቸው ተቋማት መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያም የሥራ እድል ከመፍጠር እና የአባላቱን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ የሀገርን የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ልማት የማፋጠን ሚናቸው የጎላ መሆኑን አንስተዋል።
የኅብረት ሥራ ማኅበራት ገበያን በማረጋጋት እና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በኩል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል።
ማኅበራቱ በሀገር ውስጥ ገበያ ብቻ ሳይወሰኑ የአባሎቻቸውን ምርቶች ወደ ውጭ በመላክ የክልሉን ምርቶች ለመላው ዓለም እያስተዋወቁ እንደሚገኙም አንስተዋል።
የግብይት ተሳትፏቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንደመጣ መጥቀሳቸውንም የርዕሰ መስተዳድሩ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
ሪፎርሙን ውጤታማ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ መግባባት ላይ መድረስ እና ከተለያዩ ሴክተሮች ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡