የሀገር ውስጥ ዜና

ለውጡ የህዳሴ ግድቡ ግንባታ በትክክለኛ አቅጣጫ እንዲከወን አድርጓል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን

By Tamrat Bishaw

April 02, 2024

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24፣2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራዊ ለውጡ የህዳሴ ግድቡ ግንባታ የገጠሙትን ችግሮች በማረም ግንባታው በትክክለኛ አቅጣጫ እንዲከወን አድርጓል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ዛሬ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጅማሮ የታወጀበት 13ኛ ዓመት እና የለውጡ መንግስት 6ኛ ዓመት ምስረታ የሚታሰብበት ዕለት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ማማ ለማሸጋገር ፋና ወጊ ትልም ጅማሮ ‘ሀ’ ብሎ የተጠነሰሰበት የጠቅላይ ሚኒስትራችን የለውጥ ታሪካዊ መሰረተ ድንጋይ በፓርላማ የተቀመጠው የዛሬ ስድስት ዓመት ነበር ብለዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፋይዳ እና ተምሳሌትነቱ ተፈጥሯዊ የወንዝ ውሃ ፍሰትን ለኢኮኖሚያዊ ብልጽግና የማዋል ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነ ገልጸው፤ ሀብት እያላት በድህነት ለምትማቅቀው አህጉራችን አፍሪካ ድህነትን ማሸነፍ እንደሚቻል ተስፋን የፈነጠቀ የክፍለ ዘመኑ ስኬት ነው ብለዋል።

ለኢትዮጵያውያን ደግሞ በዓድዋ ድል የአፍሪካውያንን ነፃ መውጣት በኅብረ ብሔራዊ አንድነት ትግላችው አባቶቻችን ትምህርት እንደሰጡ ሁሉ የህዳሴ ግድቡ እኛ የአባቶቻችን ልጆች ድህነትን በኅብረ ብሔራዊ አንድነት ታግለን ማሸነፍ እንደምንችል ዳግም ትምህርት የሰጠንበት በመሆኑ ኮርተናል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው የለውጥ መንግስት የህዳሴ ግድቡ ግንባታ የገጠሙትን ችግሮች ፈጥኖ በማረምና ግንባታው በትክክለኛ አቅጣጫ እንዲከወን ማድረጉን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም እየተመራች ላስመዘገበችው ዕድገት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነታችንን እያጠናከርን “ብሔራዊነትን” በማጎልበት ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ሁሌም እንተጋለን ሲሉም አንስተዋል።