የሀገር ውስጥ ዜና

የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት ፕሮጀክት እንዲሳካ አጋር እንዲሆን ተጠየቀ

By Mikias Ayele

April 04, 2024

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ከተማዋን ለነዋሪዎች ምቹ ለማደረግ ያለመ ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ተናገሩ፡፡

አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ለዲፕሎማሲ ማህበረሰቡ በሰጡት ማብራሪያ፤ የአዲስ አበባ የመንገድ ፕሮጀክት ዋና አላማው ከተማዋ በቴክኖሎጂ የላቀች እንድትሆን እና ለነዋሪዎቿ የምትመች ለማድረግ ያለመ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ከተማዋን በቴክኖሎጂ የላቀ እና ቀጣይነት ያለው ማዕከል ለማድረግ መሆኑንም ጠቅሰው፤ የከተማዋ መዘመን በከተማዋ የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ላይ የሚያስገኛቸውን አዳዲስ ጥቅሞች አብራርተዋል።

ፕሮጀክቱ በመዲናዋ የመሠረተ ልማት አውታሮችን ለማስፋፋት እና የህዝብ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል፡፡

የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቦች በተደረገላቸው ገለፃ ስለ አዲስ አበባ የመንገድ ፕሮጄክት ስትራቴጂያዊ ዓላማ ግንዛቤ እንዳገኙም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የስማርት ሲቲ ውጥን ዋና ገፅታዎች እና የመሠረተ ልማቶችን ለማሳደግ፣ የህዝብ አገልግሎቶችን ለማሻሻል እና ለነዋሪዎችና ለጎብኚዎች የበለጠ ቀልጣፋና ለኑሮ ምቹ የሆነች ከተማ ለመፍጠር ያለመ መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ታዬ፤ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ፕሮጀክቱ እንዲሳካ አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ ጠይቀዋል።