የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ 96 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የዝቅተኛ መስመር መልሶ ግንባታ ሥራ ተከናወነ

By ዮሐንስ ደርበው

April 05, 2024

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ጉለሌ ክፍለ ከተማ በስድስት ወረዳዎች የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ለመቀነስ የሚያስችል 96 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የዝቅተኛ መስመር መልሶ ግንባታ ሥራ መከናወኑ ተገለጸ፡፡

በመልሶ ግንባታና ማሻሻያ ሥራው ቀደም ሲል የነበሩትን ያረጁና የዘመሙ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎችን በማንሳት 4 ሺህ 141 አዳዲስ የእንጨት ምሰሶ ተከላ መከናወኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል፡፡

በዚህም የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥን መቀነስ መቻሉን የአገልግሎቱ መረጃ አመላክቷል፡፡

በክፍለ ከተማው በሚገኙ ቀሪ ወረዳዎች ተመሳሳይ ሥራ ለማከናወን የግብዓት አቅርቦት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ለመልሶ ግንባታ ሥራው ከ69 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ እንደሚደረግም ነው የተመላከተው፡፡