የሀገር ውስጥ ዜና

ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት ስራ ተከናውኗል

By Feven Bishaw

April 05, 2024

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ሶስት ወራት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር በላይ በሆነ መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት ስራ መከናወኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለፀ።

ባለፉት ሶስት ወራት የተሰሩ የተፋሰስ ልማት ስነ-አካላዊ ስራ አፈፃፀምና የመጪው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ዝግጅት ላይ ያተኮረ የሁሉም ክልሎች የግብርና ሀላፊዎችና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ፋኖሴ መኮንን እንደገለፁት÷ ባለፉት ሶስት ወራት በ6 ሺህ 200 ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ ዕቀባን ጨምሮ ስነ-አካላዊ ስራ ተከናውኗል።

በዚህም ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት መሸፈን መቻሉን ገልጸው፤ የስነ-አካላዊ ስራ የተከናወነበትን ተፋሰሶች በስነ-ህይወታዊ ስራ ለመሸፈን ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በዚህም 9 ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ ችግኞችን ለማዘጋጀት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በመጪው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በሀገር ደረጃ 6 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ለማሳካት ከወዲሁ ህብረተሰብ አቀፍ ንቅናቄና ተሳትፎን ለማጠናከር የሚያስችሉ ስራዎች እስከ ቀበሌ ድረስ ይሰራሉ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በመጪው ክረምት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለመትከል ከታቀደው ውስጥ 25 በመቶ የሚሆነው በዓባይ ተፋሰስ አካባቢ የሚተከሉ መሆኑንና ችግኞቹን የመለየት ስራ እየተሰራ እንደሆነ አመልክተዋል።

በተመሳሳይ ከተሞች አካባቢ የሚተከሉ ችግኞች የከተማን ውብት የሚጠብቁና መሰረተ ልማቱን የማይጎዱ እንዲሆኑ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራበት መሆኑን ጠቅሰዋል።