አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፊቼ ጨምበላላ በዓል እሴቶችን ለሀገር ግንባታ መጠቀም ይገባል ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ፡፡
የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ ፊቼ ጨምበላላ በዓል በሐዋሳ ከተማ ጉዱማሌ በተለያዩ ሁነቶች በድምቀት እየተከበረ ነው፡፡
በበዓሉ አከባበር ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የክልሉ ርስሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ እንዳሉት ፥ ፊቼ ጨምበላላ ከአምላክም ከሰውም ጋር እርቅ የሚፈፀምበት በዓል ነው፡፡
በዓሉ መለያየትና መራራቅ የሚወገዙበት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ፥ ለሰው ልጆች ሁሉ የሚጠቅመውን ሰላም ለማረጋገጥ ሁነኛ እሴት ነው ብለዋል።
በዓሉ የሲዳማ ህዝብን ማንነትና ባህል በማሳየት የቱሪዝም ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመው÷ የፊቼ ጨምበላላን እሴቶች ለሀገር ግንባታ መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በፍቼ ጨምበላላ በዓል አከባበር ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፥ፊቼ ጨምበላላ የሲዳማ ህዝብ ለኢትዮጵያ እና ለዓለም ያበረከተው እውቀት ነው ብለዋል፡፡
ፊቼ ጨምበላላ የአብሮነት፣ የአንድነትና የወንድማማችነት በዓል እንደሆነም ነው ያነሱት፡፡
የለውጡ መንግስት በኢትዮጵያ ሰማይ ስር የድህነት፣ የኋላ ቀርነትና እኔ አውቅልሃለሁ ፀሃይን አጥልቆ የእኩልነት የወንድማማችነት ፀሃይ እንድትወጣ አድርጓልም ብለዋል።
ይህ የሆነው በህዝቦች የጋራ ትግል እንደሆነም ርዕሰ መስተዳድሩ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በለውጡ አዲስ ምዕራፍ፣ አዲስ ራዕይና አዲስ ትውልድ ወደፊት እንዲራመድ እድል መፍጠሩንም ነው የገለጹት፡፡
ከሚያለያዩን ይልቅ የሚያቀራርቡን ሃሳቦች ብዙ መሆናቸውን አውቀን ፤ ያለፈውን ምዕራፍ በመዝጋት በጋራ ወደፊት መጓዝ አለበትም ብለዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ በበኩላቸው፥ ፍቼ ጨምበላላ ባህላዊ እሴቱ ሰላምን፣ አብሮነትና ወንድማማችነትን የያዘና ለሀገር ግንባታ ሰፊ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ታሪካዊና ባህላዊ እሴቱ ተጠብቆ ወደ ቀጣዩ ትውልድ እንዲሸጋገርም ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል ሚኒስትሩ።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴርም በዓሉን አስጠንቶ ማሳተሙን ጠቅሰው ፥ የፊቼ ጨምበላላን እሴቶች መተግበርና በሚገባ መንገድ መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል።
በአፈወርቅ እያዩ፣ ብርሃኑ በጋሻው እና ደብሪቱ በዛብህ