አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2016 (አፍ ቢ ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሩዋንዳ ጉብኝት ኢትዮጵያ ከሀገሪቱ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ፡፡
ቢልለኔ ስዩም የጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ልዑካቸውን የሩዋንዳ ኪጋሊ የሁለት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም ፥ ጉብኝቱ በሁለት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑን አንስተዋል፡፡
አንደኛው ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ለማድረግ ሲሆን ፤ ሁለተኛው ደግሞ ከ30 ዓመት በፊት በሩዋንዳ የደረሰውን የዘር ጭፍጨፋ መታሰቢያን ለመታደም ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኪጋሊ ቆይታቸውም በሩዋንዳ የግብርና ጥበቃ ኢንስቲትዩት ጉብኝት ማድረጋቸውን አብራርተዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ በግብርና ምርት የተሰማሩ ተማሪዎችን ተግባራዊ ስልጠና የሚያሰለጥን ሲሆን ፥ መልካም ተሞክሮ የሚወሰድበት እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡
ኢትዮጵያ ለግብርና ዘርፍ እየሰጠችው ካለው ትኩረት ጋር የሚመሳሰል መሆኑ ጠቅሰው፤እንደአብነትም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር) ተነሳሽነት ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለውን የሌማት ትሩፋት ተምሳሌት የሆኑ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ አንስተዋል፡፡
በመቀጠልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ጋር በብሔራዊ ቤተመንግስታቸው ውይይት አድርገዋል ነው ያሉት ሃላፊዋ፡፡
ባለፈው በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት ጉባዔ ላይ ሁለቱ መሪዎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ምክክር አድርገው ነበር፤ይህ ውይይትም ከዚያ የቀጠለ እንደሆነ ቢልለኔ አንስተዋል፡፡
በሁለትዮሽ ውይይታቸውም በተለያዩ ጉዳዮችን ላይ የመከሩ ሲሆን ፥ ሀገራቱ በግብርናው ዘርፍ እያደረጉ ያሉትን ጥረቶች ወደአህጉሪቱ መስፋት እንዳለበት ተጠቁሟል ብለዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩ የልዑካን ቡድን አባላት ደግሞ በየሥራ ዘርፋቸው ሀገራዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ክንውኖች አድርገዋል ነው ያሉት፡፡
የሩዋንዳ መንግስት በኪጋሊ ከተማ ለኢትዮጵያ ከ7 ሺህ 700 ካሬ ሜትር በላይ መሬት በመስጠት የኢትዮጵያ ኤምባሲ ማስጀመሪያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ መሪነት የመሰረተ ድንጋይ መቀመጡ ተገልጿል፡፡
ይህም የሁለቱን ሀገራት የስትራቴጂክ አጋር ስምምነት ግንኙነት የበለጠ ከፍ ያደርገዋል ተብሎ እንደሚታመን ነው ሃላፊዋ የተናገሩት ፡፡
በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከኪጋሊ ከተማ ከንቲባ ጋር የመግባቢያ ስምምነቶችን መፈራረማቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው ፥ 30ኛ ዓመት የሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ መታሰቢያ ሥነ-ሥርዓት ላይ መገኘታቸው ነው ተገለጸው፡፡
ፕሬዚዳንት ፖልካጋሜ በመታሰቢያው ላይ ባደረጉት ንግግር ፥ የኢትዮጵያን አጋርነት አንስተዋል፤በተለይ ከዘር ጭፍጨፋው በኋላ ኢትዮጵያ በተመድ በኩል በተዘጋጀው መልሶ የማቋቋም ስራዎች ላይ በመሳተፍ ሰላም አስከባሪ ማሰማራቷን አውስተዋል ብለዋል፡፡
ይህ የሚያሳየውም በሁለቱ ሀገራት መካከል የረጅም ጊዜ ትብብር እንደነበረ ነው ሲሉ ቢልለኔ አንስተዋል፡፡
የሁለት ቀናቱ ጉብኝትም ሀገራቱ ያላቸውን ትስስር ይበልጥ ከማጠናከር ባለፈ ለአህጉሪቱ ትሩፋት በሚሆንበት መልክ መገባደዱን ተናግረዋል፡፡
በመሰረት አወቀ