የሀገር ውስጥ ዜና

ህዝበ ሙስሊሙ ለሀገር ሰላምና ልማት የሚጠበቅበትን ግዴታ መወጣት ይገባዋል – አቶ አወል አርባ

By Tamrat Bishaw

April 09, 2024

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ህዝበ ሙስሊሙ በሀገር ሰላምና ልማት ላይ ንቁ ተሳታፊ በመሆን ግዴታውን በአግባቡ መወጣት ይኖርበታል ሲሉ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ተናገሩ።

ርዕሰ መስተዳድሩ 1 ሺህ 445ኛውን የኢድ አል-ፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ ለእስልምና እምነት ተከታዮች የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም ዒድ አል-ፈጥር ህዝበ ሙስሊሙ የመልካም ስራዎች ሁሉ ወር የሆነው የረመዳን ወርን ሸኝቶ፣ ፆሙን አፍጥሮ በደስታ፣ በመተሳሰብና በመተዛዘን የሚያከብረው በዓል መሆኑን ገልጸው፤ እንኳን በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል።

ሙስሊሞች ዒድን ሲያከብሩ መልካም ስራዎቻቸውን አላህ እንዲቀበላቸው እየተማፀኑ፣ መልካም ምኞት አንዱ ለአንዱ እየገለፀ፣ ጎረቤት፣ ምስኪኖችን፣ የተቸገሩ ወንድም እህቶችን በማሰብ ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል።

በመሆኑም የእምነቱ ተከታዮች ካላቸው በማካፈል በደስታ ማሳለፍ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በረመዳን የዳበሩትን መልካም ስራዎችንም ከረመዳን በኋላም አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ በሀገር ሰላምና ልማት ላይ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የሚጠበቅበትን ግዴታ በአግባቡ መወጣት እንደሚኖርበት አመልክተዋል።