የሀገር ውስጥ ዜና

የገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን አመራሮች የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና የስራ እንቅስቃሴን ጎበኙ

By Shambel Mihret

April 15, 2024

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን አመራሮች የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና ወቅታዊ የስራ እንቅስቃሴን መጎብኘታቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለጸ።

የገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን በኮርፖሬሽኑ በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች አተገባበርና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ የልምድ ልውውጥ አካሂዷል።

የልምድ ልውውጡ ኮርፖሬሽኑ ኢንዱስትሪ ፓርኮችንና የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠናን በማልማትና በማስተዳደር ባለፉት ዓመታት ያካበተውን እውቀትና ሰፊ ልምድ በመጠቀም በቀጣይ በተለያዩ ምዕራፎች ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀውን የገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ውጤታማ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ በዚሁ ወቅት÷ ኮርፖሬሽኑ ባለፉት ዓመታት ያካበተው የኢንዱስትሪያላይዜሽን ባህል፣ እውቀትና ልምድ ለገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ተግባራዊነት ፅኑ መሰረት የሚጥል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከወዲሁ በቅንጅት መከወን ስላለባቸው ጉዳዮች ዝርዝር ማብራሪያም መስጠታቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በቀጣይ አራት አስርት ዓመታት ውስጥ ተገንብቶ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቅ ፕሮጀክት ነው ተብሏል፡፡