የሀገር ውስጥ ዜና

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ለ1 ሺህ 460 ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ

By Melaku Gedif

April 19, 2024

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ለ1 ሺህ 460 ታራሚዎች ይቅርታ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ጎሽም÷ የክልሉ መስተዳድር ም/ቤት ሚያዚያ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ባካሄደው 6ኛ መደበኛ ስብሰባ ለ2ኛ ዙር የሚሰጠውን ይቅርታ ምክንያት በማድረግ ለ1 ሺህ 431 ወንድ እና ለ29 ሴት ታራሚዎች ይቅርታ አድርጓል ብለዋል፡፡

ይቅርታ የተደረገላቸው ተራሚዎች የፈጸሙት ወንጀል ይቅርታ የማይከለክል፣ ከተወሰነባቸው የጊዜ ቆይታ ውስጥ አንድ ሶስተኛ፣ አንድ አራተኛና አንድ አምስተኛውን የጨረሱ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ከከሳሾቻቸው ጋር እርቅ የፈጸሙ እና እድሜያቸውን መሰረት በማድረግ ይቅርታ መደረጉንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመልክቷል፡፡

ይቅርታ የተደረገላቸው ታራሚዎች ወደ ህብረተሰቡ ሲቀላቀሉ ለሌሎች አርዓያ ሆነው የተለመደ ማህበራዊ መስተጋብራቸውን ጤናማ በሆነ መንገድ ማስቀጠል እንዳለባቸው ሃላፊው አሳስበዋል፡፡