የሀገር ውስጥ ዜና

በክልሉ ምቹ ስነ-ምህዳር ለመፍጠር ህብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ

By Shambel Mihret

April 22, 2024

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የአካባቢ ብክለትን በዘላቂነት በማስወገድ ለሰዎች የተስማማ ስነ-ምህዳር ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ህብረተሰብ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ አሳሰቡ።

“ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ” በሚል መሪ ሀሳብ ብክለትን መከላከልና አካባቢ ጥበቃ ላይ ያተኮረ ክልል አቀፍ የንቅናቄ መድረክ የፌዴራል፣ የክልልና የዞን የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት በባህር ዳር ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ አረጋ ከበደ እንደገለጹት÷አካባቢን ከብክለት በመጠበቅ ለሰው ልጅ ተስማሚ የሆነ ስነ ምህዳር ለመፍጠር በተቀናጀ መንገድ መስራት ይገባል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚያዚያ ወር 2016 እስከ መስከረም 2017 ዓ.ም በሚካሄደው የአካባቢ ጥበቃ ልዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ በህብረተሰቡ ዘንድ ስለአካባቢ ጥበቃ በቂ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በየአካባቢው በዘፈቀደ የሚጣሉ ፕላስቲኮችን ዘወትር በማፅዳት አካባቢን ከብክለት ነፃ የማድረግና ስነ-ምህዳርን በዘላቂነት የመጠበቅ ሥራ የሁሉም ህብረተሰብ ኃላፊነት መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።

በከተሞች የሚስተዋለውን የፕላስትክ ቆሻሻ የማስወገድ ብቻ ሳይሆን መልሶ ጥቅም ላይ የሚውልበት መንገድ እንዲፈጠር በትኩረት እንደሚሰራ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

”ብክለት የአካባቢን ስነ-ምህዳር ከመጉዳት ባለፈ ህይወት ላላቸው አካላት ሞት መንስኤ ነው” ያሉት ደግም የክልሉ የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን አለምነህ ናቸው።