የሀገር ውስጥ ዜና

ከ40 ሚሊየን ብር በላይ የአልባሳት ግዢ ጋር ተያይዞ በሙስና ወንጀል የተከሰሱት ጥፋተኛ ተባሉ

By Shambel Mihret

April 25, 2024

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ40 ሚሊየን ብር በላይ የአልባሳት ግዢ ጋር ተያይዞ በከባድ የሙስና ወንጀል የተከሰሱት የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።

የጥፋተኝነት ፍርድ የተላለፈባቸው የቀድሞ የአዲስ አበባ እሳት እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰለሞን ፍስሃ እና ነጋዴ የሆኑት ንጉስ አማን ናቸው፡፡

ሌሎች የኮሚሽኑ ሰራተኛ የነበሩ 5 ግለሰቦች ደግሞ በተከሰሱበት ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷል፡፡

በዚሁ መዝገብ 3ኛ ተከሳሽ የነበረው የኮሚሽኑ የለውጥ ስራ አመራር ዳይሬክቶሬት ባለሙያ ደረጄ ተፈራ ነጻ ተብሏል።

ብይኑን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በ2015 ዓ.ም መጨረሻ በ8 ተከሳሾች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱ ይታወሳል።

ክሱ ተመስርቶባቸው የነበሩ 1ኛ ኮሚሽነር ሰለሞን ፍስሃ፣ 2ኛ የተቋሙ የመንግስት ግዢ ዳይሬክተር ግሩም ወልዴ፣ 3ኛ ደረጄ ተፈራ፣ 4ኛ የኮሚሽኑ የሎጂስቲክስ ምዝገባና ቁጥጥር ባለሙያ ወንድሜነህ ምስጋናው፣ 5ኛ የአደጋ ስጋት ትግበራ ቡድን መሪ እዮብ ታደሰ ካሳ፣ 6ኛ በኮሚሽኑ የህክምና ባለሙያዋ ሲስተር አልማዝ ጌቶ፣ 7ኛ የአደጋ መረጃ ሀርድ ዌርና ሶፍትዌር ባለሙያ መስፍን ለገሰና 8ኛ ንጉስ አማን ናቸው።

ከተከሳሾች መካከል 1ኛ እና 8ኛ ተከሳሾች ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ሲሆን÷ ቀሪ ተከሳሾች ግን ቀርበዋል።

ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ የተሳትፎ ደረጃ ጠቅሶ ባቀረበው የከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ላይ እንደተመላከተው በሰኔ ወር በ2014 ዓ.ም ከ1ኛ እስከ 7ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች የግዢ ጨረታ ሂደት ውስጥ በመሳተፍና በመመሳጠር፣ በወቅቱ በተደረገ የገበያ ዳሰሳ ጥናት ቡልዶዘር የተሰኘ የእሳት አደጋ መከላከያ የአልባሳት ዋጋ በፍሬ 46 ሺህ 923 ብር እያለ ተከሳሹቹ ግን በከፍተኛ ዋጋ ማለትም አንዱን 184 ሺህ 644 ብር በሆነ የገንዘብ መጠን ከ8ኛ ተከሳሽ ተጫራች ድርጅት ግዢ እንዲፈጸም አፅድቀዋል በማለት በክሱ አስፍሮ ነበር።

አጠቃላይ 217 ፍሬ አልባሳትን በ40 ሚሊየን 67 ሺህ 748 ብር ግዢ እንዲፈጸም በማድረግ በመንግስት ላይ በልዩነት 29 ሚሊየን 885 ሺህ 441 ብር ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል ብሎ በክስ ዝርዝሩ ላይ ዐቃቤ ሕግ ጠቅሶ ነበር፡፡

ከ1ኛ እና ከ8ኛ ተከሳሾቹ ውጪ ያሉ ቀሪ ተከሳሾች የክስ ዝርዝሩ ከደረሳቸው በኋላ ክሱ እንዲሻሻልላቸው የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ በጽሁፍ ማቅረባቸውን ተከትሎ የግራ ቀኝ ክርክርን ፍርድ ቤቱም መርምሮ ክሱ እንዲሻሻል የቀረበው ጥያቄ የሕግ አግባብነት የለውም በማለት ውድቅ አድርጎት ነበር።

ተከሳሾቹ የቀረበባቸው ክስ ላይ የተመላከተውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው÷ የዕምነት ክህደት ቃላቸውን በመስጠታቸው ዐቃቤ ሕግ የሰው ምስክርና የሰነድ ማስረጃ አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱም በዐቃቤ ሕግ የተሰሙ ምስክሮችን ቃልና ማስረጃ መርምሮ በዛሬው ቀጠሮ 2ኛ ተከሳሽ ግሩም ወልዴ፣ 4ኛ ተከሳሽ ወንድሜነህ ምስጋናው፣ 5ኛ እዮብ ታደሰ ካሳ፣ 6ኛ ሲስተር አልማዝ ጌቶ እና 7ኛ ተከሳሽ መስፍን ለገሰን በሚመለከት በዓቃቤ ሕግ በቀረበ ማስረጃ የወንጀል ድርጊቱ መረጋገጡን ገልጾ በተከሰሱበት ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷል።

በዚሁ መዝገብ በ3ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሰውን ደረጄ ተፈራ በሚመለከት በዐቃቤ ሕግ በቂ ማስረጃ አልተሰማበትም በማለት ፍርድ ቤቱ ነጻ ብሎታል።

በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ ችሎት ባለማቅረባቸው በጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግላቸው ትዕዛዝ ሰጥቶ ነገር ግን ችሎቱ ሳይቀርቡ የቀሩትን 1ኛ ተከሳሽ ኮሚሽነር ሰለሞን ፍስሃ እና 8ኛ ተከሳሽ ንጉስ አማንን በሚመለከት በሌሉበት የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል።

በነዚህ ጥፋተኛ በተባሉ በሁለቱ ተከሳሾች ላይ ዐቃቤ ሕግ በቀጣይ ቀጠሮ የቅጣት ማክበጃ አስተያየቱን እንዲያቀርብ ተብሏል።

ፍርድ ቤቱ ተከላከሉ የተባሉ አምስቱ ተከሳሾችን የመከላከያ ማስረጃ ካላቸው ለመጠባበቅ ለግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም ተቀጥሯል፡፡

በታሪክ አዱኛ