የሀገር ውስጥ ዜና

ጾታዊ ጥቃትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እየተባባሱ መምጣታቸውን የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አስታወቀ

By Melaku Gedif

April 25, 2024

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ፆታዊ ጥቃትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እየተባባሱ መምጣታቸውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 3ኛ ዓመት 22ኛ መደበኛ ስብሰባ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን የ2016 ዓ.ም የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትን አድምጧል።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ባቀረቡት ሪፖርት÷ ባለፉት 9 ወራት የሴቶችና ህፃናት፣ አካል ጉዳተኞችና የአረጋውያንን ተጠቃሚነትና እኩል ተሳታፊነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ሥራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።

የ16 ቀናት የፀረ-ፆታዊ ጥቃት ንቅናቄ በመፍጠር በሚሊየን ለሚቆጠሩ ዜጎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መሠራታቸውንም ነው በሪፖርታቸው ያብራሩት።

በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ምክንያት ለተጎዱ ዜጎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር መሥራታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባላትም ሪፖርቱን ካደመጡ በኋላ የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ በሴቶችና ህፃናት ላይ እየደረሱ ያሉ ፆታዊ ጥቃትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እየተባባሱ መምጣታቸውን ጠቅሰው፤ ሚኒስቴሩ ይህን ተግባር ለመከላከል ምን እየሰራ ነው ብለዋል።

የወጣቶች ስብዕና ግንባታ ማዕከላት ደረጃቸውን ያልጠበቁና የታለመላቸውን ዓላማ ለማሳካት የሚያስችል ደረጃ ላይ አለመሆናቸውንም ነው አባላቱ ያነሱት።

በሕገ-ወጥ ደላሎች ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ የሚፈልሱ ህፃናት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አመልክተው፤ ይህን ችግር ለመከላከል እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ላይ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ የሴቶች ፆታዊ ጥቃትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ማስቀረት የሚያስችሉ ጠንካራ ሕጎች እንዲኖሩ ቀደም ሲል የወጡት ላይ ጥናት በማድረግ ውጤታማነታቸው መገምገሙን ሚኒስትሯ አብራርተዋል።

ሕጎቹ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበርና ከሌሎችም አካላት ጋር የሕግ ማሻሻያ ሥራ እየተሰራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የሴት ልጅ ግርዛት፣ ያለዕድሜ ጋብቻን ጨምሮ ሌሎችም ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እና አስገድዶ መድፈርን ለማስቆም ድርጊቱን በሚፈጽሙ ግለሰቦች ላይ ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ የሕግ ማሻሻያው ወሳኝ መሆኑን ተመላክቷል፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ11 ሺህ በላይ ህፃናትን ከጎዳና ላይ በማንሳት የስነ-ልቦና ድጋፍ እንዲያገኙና ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ መደረጉንም አብራርተዋል።

በሌላ በኩል ከ90 ሺህ በላይ ለጎዳና ተዳዳሪነት ተጋላጭ የነበሩ ዜጎችን በመደገፍ ከጎዳና ህይወት መታደግ መቻሉንም ገልፀዋል።