የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ትስስር ከፍተኛ ሚና ትጫወታለች – አቶ አሕመድ ሺዴ

By Melaku Gedif

May 01, 2024

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በቀጣናው ሀገራት ደህንነትና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ዙሪያ ቁልፍ ሚና ትጫወታለች ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ ገለጹ።

አቶ አሕመድ በሳዑዲ ዓረቢያ ሪያድ በተደረገ የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም መድረክ ላይ በነበራቸው ተሳትፎ እንደገለጹት÷ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ እያደገ የመጣውን ፈተና ለመቋቋም የደቡብ ደቡብ ትብብር ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።

ኢትዮጵያ የቀጣናውን ሀገራት በማስተሳሰር ቁልፍ ሚና እንዳላት የገለጹት ሚኒስትሩ÷ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከቀረው ዓለም ጋር በማገናኘት ረገድ የአንበሳውን ድርሻ እንደሚይዝም አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ትስስርና መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገች መሆኑን ጠቁመው ÷ በአፍሪካ ቀንድ እና በዓረቡ ዓለም ግንኙተን ላይም ጉልህ ሚና እንዳላት ገልጸዋል።

ዓለም እየገጠሟት ያሉትን የተለያዩ ፈተናዎች ለመቋቋምም የደቡብ ደቡብ ትብብር ወሳኝ መሆኑንም ነው ያስገነዘቡት፡፡

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ ከዓባል ሀገራት ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንደሚያጠናክርላት አቶ አሕመድ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪከ ህብረትን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ማዕከል መሆኗን ያነሱት ሚኒስትሩ÷ ይህም በቀጣናው እና በአህጉሩ ያላት ሚና ከፍ ያለ እንዲሆን ማድረጉን ጠቁመዋል።

የብሪክስ አባል ሀገራት በኢኮኖሚ በኢንቨስትመንት በቴክኖሎጂና በአቅም ግንባታ ረገድ በትብብር መስራት የሚችሉበት ሁኔታም ሰፊ መሆኑን ገልጸዋል።