የሀገር ውስጥ ዜና

በአፋር ክልል የጎርፍ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የግድብ ግንባታ ሥራ እየተከናወነ ነው

By Melaku Gedif

May 06, 2024

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ክልል የጎርፍ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚገነቡ የግድብ መሠረተ-ልማቶች ዘላቂና የተረጋጋ ኢንቨስትመንትን ለማስቀጠል ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገለጹ።

አቶ አወል÷ የአፋር ክልል ከአርብቶ አደር ባህል ወደ ከፊል አርብቶ አደርነት በማሸጋገር ሂደት በግብርና ልማት ስኬት እየተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በርካቶች በተለይም የበቆሎ፣ ጥጥ፣ ማሽላና የስንዴ ሰብል ልማት ላይ እየተሰማሩ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከምርታማነትም ባለፈ የአርብቶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ በመቀየር ረገድ ትምህርት የተገኘበት የልማት ስኬት መሆኑን አንስተዋል።

የዘርፉ ልማት የክልሉን እምቅ የውሃ እና የመሬት አቅም በመጠቀም ምርታማ ያደረገና ከአርብቶ አደር ባህል ወደ ከፊል አርብቶ አደርነት በማሸጋገር ሂደት የላቀ አስተዋጽዖ እያደረገ ነው ብለዋል።

የክልሉ የግብርና ልማት የአርብቶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ የተሻለ ህይወት እንዲመራ እያስቻለ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

በአፋር ክልል አብዛኛው ዝቅተኛ አካባቢ ከሚኖረው የዝናብ ፍሰት በተጨማሪ በላይኛው የኢትዮጵያ ክፍል በሚመጣ ደራሽ ጎርፍ በሚያደርሰው አደጋ በኃብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርስ ገልፀዋል።

በዚህ መነሻነትም የጎርፍ አደጋን በመከላከል ለመስኖ ልማት የተገነቡት የከሰምና ተንዳሆ ግድቦች የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ጉልህ አስተዋጽዖ እያበረከቱ ነው ብለዋል።

የሎጊያ ጊጋ ወንዝ በታችኛው አዋሽ ተፋሰስ ዱብቲ፣ አሳይታና አፋምቦ አካባቢዎች የሚያስከትለውን የጎርፍ ተጋላጭነት የውሃ ፍሰት ሚዛናዊነትን የሚያስጠብቅ የግድብ ግንባታ ሥራ ተጀምሯል ብለዋል።

በመስኖና ቆላማ ሚኒስቴር ባለቤትነት በፌደራል መንግሥት የ10 ቢሊየን ብር በጀት በታችኛውና የላይኛው አዋሽ የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚሰራው የግድብ ግንባታም የአርብቶ አደሩን የግጦሽ መሬትና የሰብል ልማት ምርታማነት እንደሚያሳድግ ገልፀዋል።

በዚህም አነስተኛና መካከለኛ ግድብ ግንባታ በማከናወን በጊዜያዊነት የጎርፍ አደጋን የመከላከል በቋሚነት ደግሞ ግድቦችን የመገንባት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የጎርፍ ተጋላጭነትን የመከላከል ሥራው የመስኖ ግብርና ምርታማነትና የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት በማሰናሰል ውጤታማ ሥራ በመሠራቱ የሕዝብና መንግሥትን መተማመን የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ገልፀዋል።