የሀገር ውስጥ ዜና

አጋር ድርጅቶች ፕሮግራሞቻቸውን ከጤና ሚኒስቴር ዕቅዶች ጋር በማጣጣም እንዲተገብሩ ጥሪ ቀረበ

By Mikias Ayele

May 11, 2024

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አጋር ድርጅቶች ፕሮግራሞቻቸውን ከጤና ሚኒስቴር እቅዶች ጋር በማጣጣም እንዲተገብሩ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ጥሪ አቀረቡ፡፡

የጤና ሚኒስቴር አጋር ድርጅቶች ተወካዮች ከጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እና ከሌሎች የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ጋር የውይይት መድረክ አካሂደዋል፡፡

በውይይቱ የእናቶችን ሞት መቀነስ፣ የአፍላ ወጣቶች ተዋልዶ ጤና፣ የጤና መድህን፣ የጤና ፋይናንሲንግ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ማጠናከር፣ እንዲሁም የህክምና ግብአት እና አቅርቦት የሚኒስቴሩ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በመድረኩ ላይ እንዳስረዱት÷ የጤና አገልግሎቶችን ማጠናከር ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል።

ለዚህም ከአጋር ድርጅቶችና ከግል የጤናው ዘርፍ ጋር በቅርበት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ አጋር ድርጅቶች ፕሮግራሞቻቸውን ከሚኒስቴሩ እቅዶች ጋር በማጣጣም ሊተግበሩ ይገባል ብለዋል።

ጤና ሚኒስቴር ከአጋር ድርጅቶች ጋር በትብብር መስራቱን እንደሚቀጥል እና ለአጋር ድርጅቶች የሚደረገው ድጋፍ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው÷ አጋሮች ለሚያደርጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበው፤ በትብብሩ የተስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ ድጋፋቻውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ መጠየቃቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡