የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ የሽብር ወንጀል ለመፈጸም ሙከራ በሚያደርጉ ሃይሎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ

By Melaku Gedif

May 11, 2024

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ የሽብርና የተደራጁ ወንጀሎችን ለመፈጸም ሙከራ በሚያደርጉ ኃይሎች ላይ እየተወሰደ ያለው የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡

አገልግሎቱ ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መረጃ እንዳስታወቀው ፥ የጸጥታና የደኅንነት ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ እና አዋሳኝ አካባቢዎች የተከናወኑ የመረጃ ሥምሪቶችን ሪፖርት በአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ቀርቦ ምክክር ተካሂዶበታል።

በመድረኩ ላይ የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሑሴንን ጨምሮ የፌዴራል የጸጥታና የደኅንነት ተቋማት፣ የፍትሕ ተቋማት እንዲሁም የክልል የጸጥታ ቢሮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል ።

በመድረኩ ፥ የፀረ ሰላም ኃይሎችን የተደራጀ ሤራና ሌሎችንም ሕገ ወጥ ተግባራትን በመከላከልና በማክሸፍ ረገድ ስኬት መመዝገቡ የተመላከተ ሲሆን ፥ ይህም የጸጥታና የደኅንነት ተቋማቱ በመናበብና በተቀናጀ መንገድ ሥምሪት በማከናወናቸው የመጣ መሆኑ ተገልጿል።

በተለይ በአማራ ክልል በፋኖ ስም ሲንቀሳቀስ የነበረው ጽንፈኛ ኃይል በሀገር መከላከያ ሠራዊት እየደረሰበት ያለውን ጠንከር ያለ ምት መቋቋም አቅቶት ሲበታተን የሀገሪቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የስበት ማዕከል የሆነችውን አዲስ አበባ የጥፋት ተልዕኮው ማስፈጸሚያው ለማድረግ በኅቡዕ ተደራጅቶ ሲንቀሳቀስ ቢቆይም የቡድኑን ሰንሰለት ለመበጣጠስ መቻሉን መረጃው ጠቁሟል፡፡

በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች የሕዝቡን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማስተጓጎል እየሞከረ ባለው የሸኔ የሽብር ቡድን ላይ የተወሰደው እርምጃ የቡድኑን አከርካሪ በመስበር ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራዎች እንደደረሰበት ተነግሯል።

ከፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር ትሥሥር ያላቸው ቡድኖች በአዲስ አበባና አካባቢዋ ላይ ዝርፊያ፣ እገታና ሌሎች የተደራጁ ወንጀሎችን ለመፈጸም በኅቡዕ ለመንቀሳቀስ ቢሞክሩም፣ በጸጥታና ደኅንነት አካላት በተሠራ የተቀናጀ ክትትልና ኦፕሬሽን መክሸፉን አገልግሎቱ አመላክቷል።

በእነዚህ ወንጀሎች የተጠረጠሩ ከ174 በላይ ግለሰቦች ከተቀጣጣይ ፈንጂዎችና የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች ጋር በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንና ጉዳያቸው በሕግ እየታየ መሆኑን መግለጫው ጠቅሷል።

በተጨማሪም ሕዝብን በማማረር፣ በመመዝበርና ከጥፋት ኃይሎች ጋር በመተባበር ተግባር የተሠማሩ በገቢዎችና ጉምሩክ፣ በባንኮች፣ በፍትሕ አካላት እና በአንዳንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚሠሩ ግለሰቦችን በመረጃ ሥምሪትና ክትትል በመለየት በቁጥጥር ሥር ውለው በሕግ እንዲጠየቁ የማድረግ ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ÷ የጸጥታና የደኅንነት ተቋማቱ የጋራ ኦፕሬሽኖች በተለያዩ ክልሎች በመንቀሳቀስ በሽብር፣ በተደራጀ ስርቆት፣ በዝርፊያ እና በእገታ የወንጀል ተግባራት ላይ የተሠማሩ የጥፋት ኃይሎችን አከርካሪ ለመስበር እንዳስቻለ ተናግረዋል፡፡

ይህም አንጻራዊ ሰላም እንዲፈጠርና ኅብረተሰቡ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴው እንዲገባ ማገዙን ጠቁመዋል፡፡

የጸጥታና የደኅንነት ተቋማቱ በውስጣቸው ያሉትን ክፍተቶችና ውሱንነቶች እያረሙ የላቀ የመፈጸም ዐቅም እንዲላበሱ የሚያስችሉ ሥራዎችን አጠናክረው ይቀጥላሉ ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ፥ ተመሳሳይ መድረኮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመልክተዋል፡፡

የጸጥታና የደኅንነት ተቋማቱ በቀጣይም የተደራጁ ወንጀሎችን፣ ሽብርተኞችንና የፀረ ሰላም ኃይሎችን እንቅስቃሴ በጥናት ላይ በመመሥረት ለመከላከል የሚያግዙ ሥምሪቶች እንደሚያከናውኑ በመድረኩ የገለጹት ደግሞ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ናቸው።

አምባሳደር ሬድዋን እንዳሉት ፥ ተልዕኮን በብቃት ለመወጣትና በሕዝብ ዘንድ ቅሬታ የሚፈጥሩ ሥጋቶችን ለማስወገድ በቅድሚያ ሁሉም ተቋም ራሱን እያበቃ፣ እየፈተሸ፣ እያጠራ የመሄድ አስፈላጊነት ላይ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

መድረኩ በርካታ መልካም ተሞክሮዎች የተገኙበት መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ሬድዋን ፥ የጸጥታና የደኅንነት ተቋማቱ ራሳቸውን ከብልሹ አሠራር ለማጽዳት፤ የአባላቱን ሥነ ምግባር በቀጣይነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የሕዝብ አለኝታነታቸውን ለማስቀጠል የጀመሩትን ሪፎርም ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በተባበረና በተናበበ አኳኋን ተመሳሳይ መድረኮችን ማካሄዳቸውን እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል፡፡

በመረጃና በደኅንነት ተቋማት መካከል የሚደረገው የመረጃ ልውውጥና ሁለንተናዊ መደጋገፍ ሀገራዊ ሰላምንና ደኅንነትን በሚያረጋግጥ አግባብ እንዲመራ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንና ተመሳሳይ መድረኮችም እየተዘጋጁ አፈጻጸሞች እንደሚገመገሙም አምባሳደር ሬድዋን ተናግረዋል፡፡