የሀገር ውስጥ ዜና

በቀጣዮቹ 10 ቀናት የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ አካባቢዎች ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ

By Melaku Gedif

May 11, 2024

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀጣዮቹ 10 ቀናት የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ በርካታ አካባቢዎች ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

በዚህ መሰረትም በምስራቅ፣ በመካከለኛው በደቡብ፣ በደቡብ ምዕራብ እና በምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች በብዙ ቦታዎቻቸው ላይ ለዝናብ መፈጠር አመቺ የሆኑ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች የተሻለ ጥንካሬ እንደሚኖራቸው አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎቻችን ያመላክታሉ፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘም በደቡብ፣ በደቡብ ምዕራብ፣ በምስራቅ፣ በሰሜን ምዕራብ፣ በመካከለኛው፣ እንዲሁም በምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተሻለ የዝናብ መጠንና ስርጭት እንደሚኖራቸው ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑት የሀገሪቱ አካባቢዎች እንዲሁም በልግ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት በርካታ ቦታዎቻቸውን የሚሸፍን የተሻለ የዝናብ መጠንና ስርጭት እንደሚያገኙ ነው የተጠቆመው፡፡

በሚቀጥሉት ቀናት ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ እና ምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ፣ ቡኖ በደሌ፣ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ ጅማ፣ ኢሉባቦር፣ ምስራቅ፣ ምዕራብ፣ ደቡብ ምዕራብ እና ሰሜን ሸዋ(ሰላሌ) ዞኖች፣ ምስራቅ እና ምዕራብ ሀረርጌ፣ ቦረና እና ምስራቅ ቦረና፤ ጉጂ እና ምዕራብ ጉጂ፣ ባሌ፣ አርሲ እና ምዕራብ አርሲ የተሻለ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖራቸው ተጠቅሷል፡፡

በሌላ በኩል ከአማራ ክልል ሰሜን፣ ማዕከላዊ፣ ደቡብ እና ምዕራብ ጎንደር፣ ምስራቅ እና ምዕራብ ጎጃም፣ አዊ ዞን እና የሰሜን ሸዋ ዞኖች፤ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ፣ ካማሺ፣ መተከል እና የማኦ ኮሞ ልዩ ዞን፤ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ቤንች ሸኮ፣ ዳውሮ፣ ከፋ፣ ሸካ፣ ኮንታ እና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች፤ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባስኬቶ፣ ኮንሶ፣ አማሮ፣ ኣሌ፣ ጎፋ እና ወላይታ ዞኖች፤ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ፣ ሀላባ፣ ስልጤ እና ጠምባሮ እና የየም ልዩ ዞን ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ተጠቅሷል፡፡

እንዲሁም ከጋምቤላ ክልል ማዣንግ፣ አኝዋክ፣ የኢታንግ ልዩ ዞን እና ንዌር ዞኖች፤ ከሱማሌ ክልል ሲቲ፣ ፋፋን፣ ሊበን፤ ዳዋ፣ ሸበሌ እና ኤረር ዞኖች፤ አዲስ አበባ፣ ድሬ ዳዋ እና ሃራሪ ላይ የተሻለ የዝናብ ስርጭት ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡

በተጨማሪም ከአፋር ክልል ቂልበቲ፣ ፋንቲ፣ አውሲ፣ ሃሪ እና ገቢ ዞኖች፣ ከሱማሌ ክልል ጀረር፣ ኖጎብ፣ ዶሎ፣ ቆራሄ እና አፍዴር ዞኖች፤ ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ባሌ፤ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን፤ ከአማራ ክልል ዋህግምራ፣ ሰሜን እና ደቡብ ወሎ ዞኖች፤ ከትግራይ ክልል ምስራቅ፣ ደቡብ ምስራቅ፣ ማዕከላዊ፣ ምዕራብ እና ሰሜን ምዕራብ ዞኖች ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

ይህን ተከትሎም በሚቀጥሉት ቀናት በአባይ፣ ተከዜ፣ ባሮ አኮቦ፣ አዋሽ፣ ስምጥ ሸለቆ፣ ዋቤ ሸበሌ እና ገናሌዳዋ ተፋሰሶች ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው እርጥበት እንደሚጠበቅ ተጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል በሜይ ወር ለሚከናወኑ የበልግ ወቅት የግብርና ስራ እንቅስቃሴን በተጠናከረ ሁኔታ ለማከናወን አዎንታዊ ሚና የሚኖረው ሲሆን የሚገኘውም እርጥበት ቀደም ብለው ለተዘሩና በተለያየ የእድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ የበልግ ሰብሎችና ለቋሚ ተክሎች የውሃ ፍላጎት መሟላት እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡

እንዲሁም ቀደም ብለው የሚዘሩ የመኸር ሰብሎችን ለመዝራትና ዘግይተው ለሚዘሩ የመኸር ሰብሎች የማሳ ዝግጅት ለማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑ ነው የተመላከተው፡፡