የሀገር ውስጥ ዜና

ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ ሕዝቡ በ #ጽዱኢትዮጵያ የዲጂታል ቴሌቶን በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቀረቡ

By ዮሐንስ ደርበው

May 12, 2024

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በዛሬው ዕለት ለ #ጽዱኢትዮጵያ በአንድ ጀንበር 50 ሚሊየን ብር ለማሳባሰብ ዓልሞ በሚካሄደው የዲጂታል ቴሌቶን የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ በንቃት እንዲሳተፍ ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ ጥሪ አቀረቡ፡፡

ርዕሰ መሥተዳድሩ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ለጽዱ ኢትዮጵያችን እያዋጣን እሁድን በበጎ ተግባር እናሳልፍ ብለዋል፡፡

እንደ ክልል የጀመርነውን የጽዳት እና አካባቢን ከብክለት የመከላከል በጎ ተግባር አጠናክረን ከመቀጠል ጎን ለጎን÷ የ #ጽዱኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ የዲጂታል ቴሌቶን ዘመቻ በመቀላቀል የድርሻችንን ማበርከት ይጠበቅብናል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

ለዚህ በጎ ተግባርም መላው የክልላችን ሕዝብ የጽዱ ኢትዮጵያ ዘመቻን በመቀላቀል ዐሻራችሁን እንድታኖሩ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የቴሌቶኑ ተሳታፊዎችም በሚመቻቸው አማራጭ ቀጥለው በተቀመጡት የባንክ ሒሳብ ቁጥሮች ገንዘቡን ገቢ ማድረግ ይችላሉ፡፡

በንግድ ባንክ በተከፈተው ሂሳብ ቁጥር 1000623230248፣ በብሔራዊ ባንክ የዶላር አካውንት 0101211300016፣ በስዊፍት ኮድ NBETETAA፣ በዲጂታል ባንኪንግ ከንግድ ባንክ ወደ ንግድ ባንክ በአንድ ጊዜ 100 ሺህ ብር በቀን 6 ጊዜ መላክ ይቻላል፣ ከሌላ ባንክ ወደ ንግድ ባንክ ሲላክ ደግሞ በአንድ ጊዜ 25 ሺህ ብር በቀን 4 ጊዜ መላክ ይቻላል፡፡

የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶችን በመገንባት ክብርን ጠብቆ የመፀዳዳት ባህልን ለማዳበር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ሚያዝያ ወር ይፋ የሆነውን የ“ጽዱ ጎዳና – ኑሮ በጤና” ንቅናቄ በርካቶች በመቀላቀል ድጋፍ እያደረጉ ይገኛል።