የሀገር ውስጥ ዜና

ዋፋ ያዘጋጀው የኢትዮ-ብራዚል የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም በሳኦ-ፖሎ እየተካሄደ ነው

By Mikias Ayele

May 13, 2024

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዋፋ ማርኬቲንግና ፕሮሞሽን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የኢትዮ-ብራዚል የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም በብራዚል ሳኦ-ፖሎ እየተካሄደ ነው፡፡

ፎረሙን ዋፋ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፣ በኢትዮጵያ ከብራዚል ኤምባሲ እና በብራዚል ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ነው ያዘጋጀው፡፡

በፎረሙ በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ጣፋ ቱሉ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴዔታ ፍስሐ ይታገሱ ፣ የብራዚል የንግድ የኢንዱስትሪና አገልግሎት ሚኒስትር ጽ/ቤት ሃላፊ ማርሲዮ ኤልያስ ሮዛ እና ሌሎች የሥራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

ከዚህ ባፈም ከ250 በላይ ከኢትዮጵያ እና ብራዚል የተወጣጡ ባለሐብቶች እና ኩባንያዎች መሳተፋቸው ነው የተገለጸው፡፡

ፎረሙ ኢትዮጵያን የብራዚል ባለሃብቶችና ኩባንያዎች ዋነኛ የኢንቨስትመንት መዳረሻ በማድረግ ረገድ ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው ተመላክቷል፡፡

በተለይም በግብርና እና አግሮፕሮሰሲንግ፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በጨርቃጨርቅና በሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች ያለውን ሰፊ ዕድል መጠቀም ያስችላል ተብሏል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች ከብራዚል አቻዎቻቸው ጋር ትስስር ለመፍጠር እንዲሁም የሀገራቸውን ምርቶች በብራዚል ገበያ በስፋት ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስችል ተጠቁሟል፡፡