የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ እና አዘርባጃን የፐብሊክ ሰርቪስ ዘርፉን ቀልጣፋ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ

By Feven Bishaw

May 14, 2024

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና አዘርባጃን የፐብሊክ ሰርቪስ ዘርፉን ቀልጣፋና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሰራርን ዕውን ለማድረግ እንዲሁም ተጨማሪ ስራዎችን ተቀራርቦ ለመተግበር የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ዛሬ ቀትር አዘርባጃን መግባታቸው ይታወቃል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው እንዳሉት ÷ በአዘርባጃን የነበረን የመጀመሪያ ቀን ውሎ በተለያዩ መስኮች በጋራ መልማትና በሀገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር መንገድ የከፈተ ነው፡፡

አዘርባጃን በዲጂታል አገልግሎት በተለይም በክህሎት ማበልጸጊያ ተቋማትና የዘመነ የሲቪል ሰርቪስ ተደራሽነትን በላቀ መንገድ እየተገበረች እንደምትገኝ ገልጸው ፥ “ተዘዋውረን የጎበኘናቸው ተቋማትም ሀገሪቱ በዲጂታል ስርዓት ላቅ ያለ እምርታ ላይ እንደምትገኝ ማሳያዎች ናቸው”ሲሉ ተናግረዋል።

የፐብሊክ ሰርቪስ ዘርፉን ቀልጣፋና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሰራርን ዕውን ለማድረግ እንዲሁም ተጨማሪ ስራዎችን ተቀራርበን ለመተግበር የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመናልም ነው ያሉት።

በቀጣይ ኢትዮጵያ የጀመረቻቸውን ሁሉን አቀፍ የሪፎርም ስራዎችን በዲጂታላይዜሽን በመታገዝ የላቀ ስራን ለመተግበርና ጠንካራ የሲቪል ሰርቪስ ስርዓትን ለማረጋገጥ ከአጋር ሀገር አዘርባጃን ጋር ተቀራርበን ለመስራት ተስማምተናል ሲሉም አስታውቀዋል።