አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስር ተመስገን ጥሩነህ እና ልዑካቸው በአዘርባጃን ‘አላት’ የተሰኘ ነጻ የኢኮኖሚክ ዞንን ጎብኝተዋል፡፡
አላት’ ነጻ የኢኮኖሚክ ዞን የአዘርባጃን መንግስት የኢኮኖሚ ፕሮግራሞች ውስጥ አንዱና ዋናው ሲሆን÷ ተኪና ለዓለም አቀፍ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች በጥራትና በስፋት የሚዘጋጁበት መሆኑ ተገልጿል፡፡
በኢኮኖሚክ ዞኑ ለአምራቾች ኢንዱስትሪዎች ጥሩ የሥራ ከባቢን በመፍጠር፣ እሴትን ጨምሮ ማምረትና ፈጠራ የታከለባቸው ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ለውጪ ገበያ እንዲቀርቡ የሚደረግበት መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአዘርባጃን አልፎ የቀጠናው ”የኢንቨስትመንት እምብርት” ተብሎ ከሚጠራው ነጻ የኢኮኖሚክ ዞን ጠንካራ ተሞክሮዎች መገኘታቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
በሥፍራው ስለተደረገላቸው አቀባበልና ገለጻ የኢኮኖሚክ ዞኑን ሊቀ-መንበር ቫለህ አላስግሮቭ እና የሥራ ባልደረቦቻቸውን አመስግነዋል፡፡
ግንኙነትን በማጠናከር እና ምርጥ ልምዶችን በመቀመር ኢትዮጵያ በዘርፉ የሚጠበቅባትን እንድትፈጽም ተገቢው ክትትል እንደሚደረግም አረጋግጠዋል፡፡